ዜና፡ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1/2015 ዓ.ም፡- በጥር ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ጭማሪው ከታኅሣሥ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሊቱ 6 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ቤንዚን በሊትር – 61 ብር ከ29 ሣንቲም፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር – 67 ብር ከ30 ሣንቲም፣ ኬሮሲን በሊትር – 67 ብር ከ30 ሣንቲም ፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ – 49 ብር ከ67 ሣንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ – 48 ብር ከ70 ሣንቲም  እንዲሆን ተወስኗል፡፡ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋን በተመለከተ  67 ብር ከ91 ሣንቲም መሆኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ገልጿል። 

በአንድ ሊትር ቤንዚን ሲሰጥ የነበረው ድጎማ ከብር 15 ከ 76 ሳንቲም ወደ ብር 17 ከ 33 ሳንቲም እንዲሁም የአንድ ሊትር ናፍጣ ድጎማ ከብር 19 ከ 02 ሳንቲም ወደ ብር 22 ከ 68 ከፍ እንዲል መደረጉ ተገልጧል፡፡

የትራንስፖርት ክፍያ ምክንያት በክልል ከተሞች ላይ የዋጋ ልዩነት እንደሚኖር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተልጧል።

የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ በሚመለከት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ማስታወቂያ እንዳዘጋጀ እና በዚሁ የሕዝብ ማስታወቂያ የተካተቱ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በዝርዝር ጥር 01 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ማደያዎች ሁሉ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጿል።

መስከረም 18/2015 ዓ.ም በተደረገው ጭማሪ በአዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ቤንዚን በሊትር – 57 ብር ከ05 ሣንቲም ፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር – 59 ብር ከ90 ሣንቲም እና ኬሮሲን በሊትር -59 ብር ከ90 ሣንቲም ሲሸጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያው የመንግስትን ወርሃዊ ኪሳራ ከ10 ቢሊዮን ወደ 4 ቢሊዮን ብር ዝቅ እንዲል ማድረጉን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ህዳር ወር ላይ አስታውቋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.