በሚሊዮን በየነ @millionbeyene
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23/ 2015 ዓ.ም፡- የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) የትግራይ ክልል ከእኛ የሚጠይቀው ጉዳይ ካለ በሰላም፣ በውይይት ከዚያም ባለፈ በህግ አግባብ መፍታት እንችላለን ሲሉ ተናገሩ፡፡ የአማራ ክልል ህዝብ ከወንድሙ የትግራይ ህዝብ ጋር የሚያጋጥመውን ችግር በሰላም እና በድርድር ለመፍታት ነው የሚዘጋጀውም፣ የሚያስበውም ብለዋል።
ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ይህን ያሉት ከክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ነው። ርዕሰ መስተዳድሩ ልዩነት እና ችግር ካለ በሰላም በውይይት እና በህግ አግባብ መፍታት የምንችልበትን የሰለጠነ አካሄድ መያዝ እና መጠበቅ ይገባል ብየ አስባለሁ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
“ስንዋጋ የነበረው የአንድ ሀገር ዜጎች ነን፣ ወንድማማች ህዝቦች ነን፣ መደረግ መፈጸም ያልነበረበት ዋጋ ሁለታችንን ጎድቷል” ያሉት ይልቃል ከፋለ ቀጥለውም እስካሁን ባደረግነው ጦርነት የትግራይም ሆነ የአማራ ህዝብ ከስቃይ፣ ከመከራ፣ ከስደት በስተቀር ያተረፈው ነገር የለም፤ ይሄ ያላስተማረው ሌላ ማን ከየት መጥቶ ሊያስተምረው ይችላል ሲሉ ጠይቀዋል። ጦርነትን በቻልነው መንገድ ማስቀረት እና ማስወገድ አለብን ብየ አስባለሁ ሲሉም ተደምጧል፡፡
ቀድሞውንም ቢሆን እንደዚህ አይነት ችግሮች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተፈትተው ቢሆን፣ በድርድር እና በውይይት ተፈትተው ቢሆን፣ በሽምግልና እና በሰለጠነ መንገድ ተፈትተው ቢሆን የዚህ አይነት ችግር እና ምስቅልቅል በሀገራችን ላይደርስ ይችል ነበር ብለን እናስባለን ያሉት ይልቃል ከፋለ ነገር ግን በባለፈው ላይ አሁንም ቁመን በመወጋገዝ ጊዜውን ማሳለፍ የለብንም፤ የወደፊቱን ማየት አለብን፤ ሲሉ አሳስበዋል።
ፕሪቶርያ ላይ ስምምነት መካሄዱን እና በስምምነቱ መሰረት በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን ከፍተኛ ርቀት መኬዱን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ የሰላም አፈጻጸሙ ምን ይመስላል የሚለውን ጉዳይ በዝርዝር በፌደራል መንግስት የሚገመገም እና የሚገለጽ እንደሚሆን አስታውቀዋል። በሰላም ስምምነቱ መሰረት ይሄ ሀገር ሰላም እንዲያገኝ በዚህ አከባቢ ምን ምን ማድረግ እንዳለበት የፌደራል መንግስት የራሱን ክትትል እና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በሀገረ መንግስት ግንባታው ማህበረሰቡ ገና ያልተግባባባቸው ወሳኝ ገዢ ሀሳቦች መኖራቸውን እና አሁን ያለው መንግስት የሀገሪቱ ህዝቦች ተግባብተው የተቀበሉት፣ የፈለጉት መንግስት ነው ለማለት በሚያስችለን ሁኔታ ላይ አይደለንም ሲሉ ተደምጠዋል። አክለውም ሀገረ መንግስት ግንባታው ገና አልተጠናቀቀም ብለዋል። በጉልበት የሚመጣ የሀገር ግንባታ ሊኖር አይችልም ሲሉ ገልጸዋል።
ከቀናት በፊት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ለክልሉ የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ በርካታ የትግራይ ግዛቶች አሁንም በኤርትራ እና በአማራ ታጣቂዎች በጉልበት ተይዘዋል ሲሉ መናገራቸው ይታወቃል፡፡ አቶ ጌታቸው “አሁንም በነዋሪዎቹ ላይ ከፍተኛ ግፍ በመፈጸም ላይ ነው፤ ይህንን የማስቆም ሃላፊነት የፌደራል መንግስቱ ግዴታ ነው” ብለዋል።
ይህንን በተመለከተ ርዕሰ መስተዳደሩ ይልቃል ከፋለ ያሉት ነገር የለም፡፡ በሁለቱ አካላት መካከል ፕሪቶርያ በተደረሰው ስምምነት መሰረት የፌዴራሉ መንግስት ግዛቶቹን የማስለቀቅ ሀላፊነት እንደተጣለበት ይታወቃል፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ በተመሳሳይ ለክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ ጎረቤት ከሆነው የአማራ ክልል መንግስት ጋር ያሉብንን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ነን ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል። በወቅቱ አቶ ጌታቸው ከጎረቤቶቻችን ጋር ብዙ ተዳምተናል፣ ይሄ መቀጠል አይችልም፤ ከስሜት በጸዳ መልኩ በሰላማዊ መንገድ በህጋዊ እና በህገመንግስታዊ መንገድ እየከበደንም ቢሆን መልመዱ የሚያዋጣነው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
አሁንም የሚታዩት ችግሮች በትግራይ ህዝብ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እንደተጠበቀ ሁኖ በሀገር ደረጃ የሚታየው የሰላም ጭላንጭል አደብዝዞ ወደ ለየለት ቁሩቁስ ለመግባት ከመፍጠር አንጻር ያለው ትርጉም ከፍተኛ በመሆኑ በፌደራል መንግስትም፣ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብም ዘንድ እና ከምንም ነገር በላይ ወንድም በሆነው የአማራ ህዝብ ዘንድ ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት እልባት ሊያገኝ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። ግጭቱን ያስቆምነው ተመልሰን ወደ ግጭት ለመግባት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ነገሮች እንዲፈቱ ለማድረግ ነው ብለውም ነበር።አስ