ዜና፡ የጤና ሚኒስቴር በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር  1.2 ሚሊዮን የኮሌራ ክትባቶችን ጠየቀ

ፎቶ-Save the Children

አዲስ አበባ፣መጋቢት 25፣2015 ዓ.ም፡- የጤና ሚኒስቴር በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች እየተከሰተ ያለውን የኮሌራ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር  1 ነጥብ 2 ሚሊየን የኮሌራ ክትባቶችን ከአለም ጤና ድርጅት ጠየቀ።

የአሁኑ ወረርሽኝ በኦሮሚያ ክልል ሀረናቡሉክ ወረዳ  ከተከሰተበት ባለፈው አመት ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በአራት ዞኖች ማለትም በባሌ ፣ በጉጂ ፣ በምዕራብ አርሲ እና በምስራቅ ባሌ ውስጥ በሚገኙ 18 ወረዳዎች እንዲሁም በሶማሌ ክልል 4 ወረዳዎች ላይ በአጠቃይ 22 ወረዳዎች ላይ ተከስቷል፡፡

በኦሮሚያ ሶስት ወረዳዎች እና በሱማሌ ሁለት ወረዳዎች ላይ የተከሰተዉን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የተቻለ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት 18 ወረዳዎች ላይ ወረርሽኙ እየተከሰተ መሆኑን የሚኒስቴሩ መግለጫ ገልጿል።

የኮሌራ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ሁሉም ወረዳዎች  23  ጊዜያዊ የኮሌራ ህክምና መስጫ ማዕከላት መቋቋሙን የገለፀው መግለጫው የህክምና ግብዓቶች ለማዕከላቱ በማሰራጨት ተገቢው አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛሉ ብሏል።

በኦሮሚያ እና በሶማሊ ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የኮሌራ ክትባትን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ያለው መግለጫው ወረርሽኝ ለተከሰተባቸው እና ለአጎራባች ወረዳዎች 1.2 ሚሊዮን የኮሌራ ክትባት ለአለም ጤና ድርጅት ተጠይቆ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ሲል አክሏል።

ባለፈው ሳምንት ወደ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂ እና ቦረና ዞኖች እንዲሁም ሶማሌ ክልል በዳዋ ዞን የተስፋፋው የኮሌራ ወረርሽኝ እስከ መጋቢት 23 ቀን 2023 የሟቾችን ቁጥር ወደ 50 ከፍ እንዲል በማድረግ አጠቃላይ የኮሌራ ተጠቂዎችን ደግሞ ወደ 2,276 አድርሷል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት አስታውቋልአስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.