አዲስ አበባ ፣ መስከረም 3፣ 2015 ዓ.ም፦ የትግራይ ክልላዊ መንግስት በአፍሪካ ህብረት “የጋራ ተቀባይነት ባላቸው ሸምጋዮች” የሚመራውን የሰላም ሂደት “በአፋጣኝና በጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ የጦር አቁም” ማዕቀፍ መቀበሉን የነጩ ቤተ መንግስት በደስታ መቀበሉን አስታወቀ።
እሑድ መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሎች ሀገራት እና ተቋማት በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት የትግራይ ክልል መንግስት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ታማኝነት ያለው የሰላም ሂደት ለመሳተፍ መዘጋጀቱን አስመልክተው አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።
የክልሉ መንግስት የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳን፣የክልሉን ፕሬዚደንት ደብረፂዮን ገብረሚካኤልን (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዋና ኢታማዦር ሹም የነበሩትን ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ የድርድር ቡድኑ አድርጎ የሰየመ ሲሆን “ ወደ ድርድሩ ሳይዘገዩ ሊሰማሩ ተዘጋጅቷል” ሲልም አክሏል።
ዋይት ሀውስ ሰኞ መስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም በሰሜን ኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ሃይሎች የአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት እንደሚቀበሉ የገለፁትን መግለጫ በበጎ እንደተመለከተው ገልጿል።
የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን ፒየር ኤር ፎርስ 1 ሚድያ ላይ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ሁለቱም ወገኖች ጦርነታቸውን አቁመው ወደ ውይይት የሚመለሱበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል። “ኢትዮጵያ ይህንን ጊዜ ተጠቅማ ለሰላም ዕድል መስጠት አለባት” ያሉ ሲሆን “ኤርትራም ሆነች ሌሎች ከግጭት መራቅ አለባቸው” ሲሉም አክለዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ክልል መንግስት በአፍሪካ ህብረት የሽምግልና ሚና ላይ ልዩነቶችን አሳይተዋል። የፌደራል መንግስቱ የአፍሪካ ኅብረትን ለዓለም አቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ”ብቸኛው አህጉራዊ መንገድ “ በማለት በተደጋጋሚ በአፅኖት ሲያስታውቅ የቆየ ሲሆን በሌላ በኩል የትግራይ ክልላዊ መንግስት ደግሞ “በትግራይ ህዝብ እና መንግስት ግምት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ያሉበትን የአመራር ውድቀቶች እና ያለንን አመኔታ መመለስ አለበት ” ሲል እንደነበር ይታወቃል።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ የፌደራል መንግስት በእሁዱ የትግራይ ክልል መንግስት መግለጫ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም። አስ