አዲስ አበባ፣ጳጉሜ 1፣ 2014 ዓ.ም፦ በኢትዮጵያ የሚገኙ ጀማሪ (ስታርት አፕ) የቴክኖሎጂ ተቋማትን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ዐውደ ጥናት ተካሄደ፡፡
በኢትዮጵያ ጀርመን ትብብር ፕሮጀክት እውን የሚሆነው ይህ ድጋፍ ድርጅቶቹ ለሀገር የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ በእጅጉ ከፍ እንደሚያደርገው ተነግሯል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ወርቁ ጋቸና ዓለም በቴክኖሎጂው እድገት እየተጠቀመ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ይህን ጥቅም የበለጠ ከፍ ለማድረግ ጀማሪዎችን መደገፍ እና ማበረታታት ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዙሪያ የሚሰሩ ጀማሪዎችን ለማበረታታት በኢንስቲትዩቱ ሁለንተናዊ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በተጨማሪም የጀርመን መንግስት ለጀማሪዎች ድጋፍ የሚውል ትብብር በማድረጉ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጀርመን ትብብር ፕሮጀክት ማናጀር ዶ/ር እንድሪያስ ጎይዶር በበኩላቸው ጀማሪ (ስታርት አፕ) የቴክኖሎጂ ድርጅቶቹ ውጤታማ እስኪሆኑ ድረስ የጀርመን መንግስት ድጋፍ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
እንደ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንሽ እንስቲቱዩት ማብራሪያ መሠረት በመድረኩ የኢትዮጵያ እና ጀርመን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ አተገባበር ሂደትን የሚያሳይ የውይይት ሰነድ ቀርቦ የልምድ ልውውጥ ተደርጓል፡፡