አዲስ አበባ፣ ህዳር 16/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የአገልግሎት ክፍያ እና ቅጣት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ተቃዉሞ ቢገጥመዉም ህግ ሆኖ ፀደቀ፡፡ የቴለቪዥን ሚዲያውን እንደገና ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ የተካተተው የአገልግሎት ክፊያና ቅጣት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባልተለመደ መልኩ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡
አባላቱ ሃሳባቸውን የገለፁት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባው የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም በሚል ባቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሐሙስ ዕለት በተደረገ ውይይት ነው፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከህዝብ የአገልግሎት ክፊያን ለመሰብሰብ በረቂቅ አዋጁ ከአንቀፅ 17 ጀምሮ ያቀረበው የክፊያና የቅጣት አንቀፆች ተገቢነት እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡
በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዜጎች በመኖሪያ ቤታቸው በሚያገኙት የአንድ ቴሌቪዥን አገልግሎት 1 መቶ 20 ብር በዓመት መክፈል እንሚኖርባቸው የሚደነግግ ሆኖ ከአንድ በላይ ቴሌቪዥን ያላቸው ከሆነ ደግሞ ባላቸው የቴሌቪዥን ብዛት ተሰልቶ ይከፍላሉ ይላላል፡፡
ረቂቁ አያይዞም ይህንን በማያደርጉ ዜጎች ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት እስራት ወይም ደግሞ ከአንድ ሺ እስከ አምስት ሺህ ብር ቅጣት እንዲጣልባቸው ይደነግጋል፡፡
ለንግድ ቤቶችም ክፊያው እንዳለ ሆኖ ህጉን ካላከበሩ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ጋር በሚደረግ ስምምነት መሰረት የንግድ ፈቃዳቸው እንዳይታደስ ይደረጋል በሚል ተደንግጓል፡፡
የምክር ቤት አባላት ተቃውሟቸውን አቅርበዋል፡፡ ተቋሙ የሚሸጥ ገንዘብ ሊያመጣ የሚችል ነገር መስራት አለበት፤ ህዝብ መርጦት ሊከታተለው የሚችል ሳቢና ወቅታዊ የሆነ መረጃ በማቅረብ ተወዳዳሪ መሆን ስላልቻለ የአግልግሎት ክፊያ መጠየቅ ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡ አባላቱ አያይዘውም ከንግድ ፈቃድ እድሳት ጋርም መያያዝ የለበትም ብለዋል፡፡
አቶ ኢተፋ ኢብሳ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል “የአገልግሎት ክፊያው ከንግድ ፈቃድ መታደስ ጋር መያያዝ የለበትም፡፡ ንግድ ፈቃድ አይታደስም የሚለው አግባብነት የለውም አንድን የተለየ ዘርፍ ከሌላ ጋር እያዳበልን የሚናስተላልፈው የቅጣት ውሳኔ እጅጉን ጎጂ ነው” ብለዋል፡፡
አባሉ አያይዘውም እንደዚህ ዓይነት ቅጣቶችን ከማስተላለፍ አገልግሎትን የማቋረጥ እርምጃ ቢወሰድ የተሻለ ይሆናል ሲሉም አማራጭ ያሉትን ሃሳብ ተናግረዋል፡፡
የምክር ቤት አባል አቶ አሰማሀኝ አስረስ በበኩላቸዉ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በየግዜው ከሚፈጠር ስርዓትና ፖለቲካ ጋር እየተለጠፈ ዥዋዥዌ የሚረግጥ እንጂ ከተቋቋመ ጀምሮ ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት እዚህ ግባ የሚባል የጋዜጠኝነት ስራ አልሰራም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
ገንቢ የሆነ የጋዜጠኝነት ስራ አለመስራቱ የመነጨው ከገንዘብ ችግር አይደለም ያሉት አባሉ የአመለካከት የአስተሳሰብና የስነምግባር ችግሮች ጎልተው እንደሚታዩበት ተናግዋል፡፡ “እስካሁን ባሳለፋቸው ዓመታት በየግዜው ለሚፈጠር ፖለቲካ አፈቀላጤ ሆኖ እያገለገለ ያለ በመሆኑ አሁን ይህንን አዋጅ ብናፀድቅም መፍትሄ አያመጣም” ነው ያሉት፡፡
አባሉ አያይዘውም “በአሁኑ ወቅት ትክክለኛ መረጃ እየሰጠ መሆኑን መጠየቅ ይኖርብናል ከፖለቲካ ተፅእኖ ነፃ ሆኖ እየሰራ አይደለም እየተከተልነው ባለን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መሰረት ለሁሉም በእኩል ተደራሽነት ኖሮት አይሰራም ከሌሎች ሚዲያዎች ጋርም ተወዳዳሪ ሚዲያ መሆን አልቻለም” ብለዋል፡፡
የምክር ቤት አባል አቶ ነጋሽ ቡላላ በበኩላቸው “ህዝቡን ክፈል የሚንለው ለገዛው እቃ ካልሆነ በስተቀር ተቋሙ ክፊያ ለመጠየቅ የሚያስችልና ተወዳዳሪ የሚያደርገው የሚዲያ ስራዎችን ለህዝብ እያቀረበ አይደለም” በለዋል፡፡
ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላች ተቋሙ ከግዜ ወደ ጊዜ የሚያስተላልፋቸው ፕሮገራሞች አድማጭ እያጡ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ከህዝብ ገንዘብ እንዲሰበስብ አዋጅ ማፅደቅ ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡
“ዝግጅቶቹን ተወዳዳሪ አድርጎ ተመራጭ መሆን ይኖርበታል፡፡ በአንድ ካሜራና በጠባብ ክፍል ተፅእኖ ፈጣሪ እየሆኑ የመጡ ሚዲያዎችና ዩቱዩበሮች አሉ፡፡ ይህ ተቋም ግን ባለው አደረጃጀትና በሚመደብለት ባጀት ሙያውን ማሻሻልና ተወዳዳሪ መሆን ካልቻለ ህዝብን እያስለቀስን ገንዘብ እንዲሰበስብ ሊንፈቅድ አይገባም” ብለዋል፡፡
ተቋሙ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዴት ይገመግመኛል ብሎ ማጥናት ይኖርበታል ያሉት አባላቱ የህዝብ ተቋም ሆኖ አብዛኛውን ሰዓት ለአንድ ቋንቋ ብቻ ይጠቀማል፤ እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብና ህዝብ በራሱ ቋንቋ ለተወሰነ ደቂቃዎች ሊያቀርብለት ላልቻለ ተቋም አገልግሎት ክፊያ ተጥሎብሃል ማለት ተገቢነት አይኖረውም ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑን እንደገና ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዉስጥ የተካተተዉ የአገልግሎት ክፊያና ቅጣት ከምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ተቃዉሞ ቢገጥመዉም በመጨረሻ በ44 ተቃውሞና በ24 ድምፀ ተቅቦ አዋጅ ቁጥር 1278/2015 ሆኖ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡ አስ