አዲስ አበባ፣ጥር 26/ 2015 ዓ.ም፡– የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መርማሪ ቡድን በኢትዮጵያ ስልጣን እና ተግባሩ እንዲቋረጥ ኢትዮጵያ የአሜሪካንን ድጋፍ ጠየቀች።
ኢትዮጵያ ጥሪውን ያቀረበችው ትላንት የአሜሪካን ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑት አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን ጋር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ምስጋኑ አረጋ በተወያዩበት ውቅት መሆኑን ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ገጹ ያሰፈረው መረጃ አስታውቋል። በውይይታቸውም ወቅት አምባሳደር ምስጋና የአሜሪካ መንግስ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ መንግስት እና በህውሓት ሀይሎች መካከል በፕሪቶርያ የተደረገውን ስምምነት እንዲፈጸም ላደረገችው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል። በተጨማሪም አምባሳደር ምስጋና መንግስት ለስምምነቱ ተግባራዊነት አጥብቆ እንደሚሰራ መግለጻቸውን መረጃው አመላክቷል። የአሜሪካ የመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ጥረቶችን እንድትደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሽግግር ፍትህ ስርዓት መሰረት በማካሄድ ለመፍታተ ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደሩ በእጽንኦት ገልጸው የፖለቲካ አላማው የሚያመዝነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መርማሪ ቡድንን በኢትዮጵያ ስልጣን እና ተግባሩ እንዲቋረጥ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት አሜሪካ ድጋፍ እንድትሰጥ መጠየቃቸውን መረጃው አስታውቋል።
ባሳለፍነው ታህሳስ ወር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አምስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ለኮሚሽኑ ምንም አይነት ድጋፍ እንዳይደረግለት እና እንዳይጸድቅለት ያቀረበችውን የውሳኔ ሃሳብ የአባላቱ ሀገራት በ71 ተቃውሞ በ32 ድጋፍ እና 50 ሀገራት ድምጸ ተአቅቦ ውድቅ እንደተደረገባት ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መርማሪ ቡድን በኢትዮጵያ ባሳለፍነው አመት መስከረም ላይ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ካውንስል የመጀመሪያ ግኝቱ ማቅረቡ ይታወሳል።
በመጀመሪያ ግኝቱም ባቀረበው ውሳኔ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ጀምሮ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ አሳማኝ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቁሞ የተፈጸሙት ጥሰቶችም ከህግ ውጭ የሆነ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ጾታዊ ጥቃት፣ ንጹሃንን ሆን ብሎ ማስራብ እንደጦር መሳሪያ መጠቀም የሚሉት ይገኙበታል። በመሆኑም ከተፈጸሙት ወንጀሎች በመነሳት በሰብዓዊነት የተፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው ብሎ ለመውሰድ በቂ ምክንያቶች አሉ ማለቱ ይታወቃል።
ከቡድኑ ምስረታ ታህሳስ 8 ቀን 2014 ዓም ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡድኑ የተቋቋመው ለፖለቲካዊ አላማ ነው በሚል ግንኙነቷ የሻከረ እንደነበር ይታወሳል። ኢትዮጵያ ቡድኑን ሰብዓዊ መብትን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ለፖለቲካዊ ግፊት ለማድረግ የተቋቋመ ነው ስትል ስትኮንነው ነበር።
የአምሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት በሰጠው መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፒራይ አሜሪካ ግጭትን ለማቆም የተስማሙትን አካላት በማመስገን በአለም አቀፍ የአብዓዊ መብቶች ክትትል የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እና የፍትህ ሽግግርን ትግበራ ታበረታታለች ብለዋል፡፡አስ