ዜና፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ በረራዎች እንዲፋጠኑ መመሪያ ሰጡ- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

አዲስ አበባ፣ ጥር 27/ 2015 ዓ.ም፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ በረራዎችን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች እንዲፋጠኑ መመሪያ መስጠታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ክልሉ የሚደረጉ በረራዎች እንዲጨምሩ፣ የባንክ አገልግሎት እንዲፋጠን እና ሌሎች እርስ በርስ መተማመንን የሚያጎለብቱ እና የዜጎችን አኗኗር የሚያቀሉ አገልግሎቶች እንዲፋጠኑ መመሪያ ማስተላለፋቸውን ነው የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት።

የፌዴራል መንግሥት እና የህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዜ በትላንትናው ዕለት በሐላላ ኬላ ተገናኝተው ምክክር አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰላም ስምምነት ትግበራ አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር ባደረጉት ውይይት እስካሁን በሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራት ተገምግመዋል፡፡

በቀጣይም ትኩረት በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የሰላም ድርድሩ ኮሚቴ አስተባባሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመጀመሪያውን የገፅ ለገፅ ግንኙነት ያደረጉት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል በሆነው ሃላላ ኬላ ነው፡፡

ምንጭ- ፋና

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.