አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 23፣ 2015 – የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ (ሲፌፓ) ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሙሉ እውቅናና ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ ተመዘገበ።
ይህን ተከትሎም ፓርቲው የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ለመላው አመራሮች፣ አባላቶች፣ ደጋፊዎችና አጋሮች፣ እንዲሁም ለመላው የሲዳማ ህዝብ አስተላልፏል።
ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ጊዜያዊ የምዝገባ ፍቃድ የተሰጠው የሲዳማ ህዝብን በዋና ምርጫ ክልልነት የሚወክለው ሲፌፓ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው የምስረታ ጉባኤ ሊቀመንበር እና ስራ አስፈፃሚ ኃላፊዎችን በመምረጥ በይፋ መመስረቱን አሳውቖ ነበር።
በዚህም መሰረት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትን ተሰማ ኤልያስ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው በወቅቱ መመረጣቸው የሚታወስ ነው፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ለሲዳማ ክልል የሲዳማ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ትግልን በመደገፍ የሚታወቁ ሲሆን በሲዳማ ክልል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ለአንድ አመት ያህል ታስረው የነበሩ ፖለቲከኛ ናቸው።
ሲፌፓ የሲዳማ ህዝብ ትግል መሰረታዊ ዓላማን እውን ለማድረግና ህዝቡ እየደረሰበት ያለውን ችግር ለመቅረፍ ህዝቡን አደራጅቶ የሚታገል ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ባለመኖሩ ህዝቡ ለከፋ ችግር እንዳይጋለጥ ጥቅሙን የሚያስከብረለት ተገዳዳሪ ፓርቲ ያስፈልጋል በሚል መርህ የተመሠረተ ፓርቲ ሲሆን፣ “በዴሞክራሲያዊ እሴቶች፣ ዴሞክራሲያዊና ህዝባዊ የስልጣን ባለቤትነትን ተግባራዊ ለማድረግ ለመታገል፣ በብዝሃነት እና በውይይት በማመን፣ እውነተኛ ሀገራዊ ፌደራሊዝምን በመከተል እውን ለማድረግ ተመሳሳይ ግብ ካላቸው ብሄራዊ ፓርቲዎች ጋር ይሰራል” ሲል የፓርቲውን አስፈላጊነት ገልጿል።
በህዳር 2011 ዓ.ም በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ መራጮች በአብላጫ ድምጽ የሰጡበት የሲዳማ ክልል የኢትዮጵያ 10ኛ ክልላዊ መንግስት መሆኑ ይታወሳል ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክልሉ በገዢው ብልፅግና ፓርቲ እየተተዳደረ ይገኛል። አስ