ዜና፡ የሱዳን ቀውስ ጎረቤቶቿን አስጨንቋል፤ ሀያላኑን አሳስቧል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14/2015 ዓ.ም፡- አንድ ሳምንት ያስቆጠረው የሱዳን ቀውስ ጎረቤተሮቿን ከማስጨነቁ ባለፈ ሀያላን ሀገራትን አሳስቧል። ሮይተርስ የዜና ወኪል ያስነበበው ትንታኔ እንደሚያመላክተው የሱዳን ጎረቤቶች እና ሃያላኑ ሀገራት በየራሳቸው ምክንያቶች ሁኔታውን በትኩረት በመከታተል ይገኛሉ። ግብጽ በናይል ውሃ ያላት ጥቅም፣ ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ጉዳይ፣ ሀያላኑ ሀገራት በቀጣይ የሚመሰረተው የሱዳን መንግስት ምን አይነት ቅርጽ ይኖረዋል፣ አሰላለፉ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ፣ የአውሮፓ ሀገራት ስደተኛ ሊመጣብን ይችላል የሚል ስጋት፣ ሌሎች ደግሞ የሚፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ እንዳስጨነቃቸው እና እንዳሳሰባቸው በዝርዝር ተቀምጧል።

ከሰባቱ የሱዳን አጎራባች ሀገራት መካከል አምስቱ ኢትዮጵያ፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ሊቢያ እና ደቡብ ሱዳን በራሳቸው ምክንያት ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በፖለቲካ አለመረጋጋት እና በግጭት ቀውስ ውስጥ ማለፋቸውን የዜና አውታሩ ዘገባ አመላክቷል።

በጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የአገሪቱ መከላከያ ሀይል እና በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሀይል መካከል ካርቱምን ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች ውጊያ መካሄድ የጀመረው ከአንድ ሳምንት በፊት ሚያዚያ 7 ቀን 2015 መሆኑ ይታወሳል። 

የሱዳን አጎራባች ሀገራትን ያሳሰባቸው ምንድን ነው ሲል የጠየቀው ሮይተርስ የዜና ወኪል የሚከተለው ትንታኔ አስነብቧል።

ግብጽ

ግብጽ እና ሱዳን በንግድ፣ ባህል፣ ፖለቲካ እና ናይል ውሃ በጋራ የተሳሰሩ ሀገራት ናቸው። ግብጽ የሱዳን ሁኔታ ሊያስጨንቃት የጀመረው በተለይ የቀድሞ የሱዳን መሪ ኡመር አልበሽር በመፈንቅለ መንግስት ከወንበራቸው ከተወገዱ ከ2019 በኋላ መሆኑ ተገልጿል። በጦር ሰራዊቱ አጋዥነት ወደ ስልጣን የመጡት የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ የአልቡርሃን የቅርበ ወዳጅ ናቸው። በግብጽ ከሚገኙ የውጭ ሀገር ተወላጆች ትልቁን ቁጥር የሚይዙት ሱዳናውያን ሲሆኑ አራት ሚሊየን ይጠጋሉ ተብሎ ይገመታል፤ ከእነዚህ ውስጥም ስድስት መቶ ሺ የሚሆኑት ስደተኞች እና ጥገኝነት የጠየቁ ናቸው። ግብጽ እና ሱዳን የናይል ውሃ ጥገኞች ናቸው፤ በኢትዮጵያ የሚገነባው የህዳሴ ግድብ በሚያገኙት ውሃ ላይ እጥረት ይፈጥርብናል የሚል የጋራ ስጋት አላቸው።

በግብጽ በኩል የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አሁን ሱዳን ላይ የተፈጠረው ቀውስ እንዳያበላሸው ስጋት ያሳደረባት ከሱዳን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ሊያደናቅፈው ስለሚችል ነው።

ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር በተለያዩ ግዜያት ግጭት ይፈጠራል። በሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን ለማስከበር ስትል ልትጠቀምበት ትችላለች የሚል ስጋት በተንታኞች በኩል እየተስተዋለ ይገኛል። በ2020 በትግራይ ተፈጥሮ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል የይገባኛ ጥያቄ በሚቀርብበት አልፋሽቃ ምክንያት ውጥረት ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል። በጦርነቱም ከ50ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን ተሰደዋል። ሱዳን በወቅቱ በርካታ ኪሎሜትሮችን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመግባት የአልፋሽቃ አከባቢዎችን መቆጣጠሯ ይታወሳል።

ከአልፋሽቃ ለም መሬት በተጨማሪ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያ የሱዳንን ሁኔታ በትኩረት እንድትከታተለው አስገድዷታል።

ኤርትራ

ከ134ሺ በላይ የኤርትራ ስደተኞች በሱዳን ተጠልለው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ። በኤርትራ መንግስት አስገዳጅነት የሚካሄደውን የዜጎች የወታደራዊ ግዳጅ ለመሸሽ ኤርትራውያን የሚጠቀሙት ዋነኛ ማምለጫ መንገድ ወደ ሱዳን መሰደድ ነው። በትግራዩ ጦርነት በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ኤርትራውያን የተሰደዱት ወደ ሱዳን እንደነበር ይታወሳል።

በተመሳሳይ በሱዳን ያለው ቀውስ ከተባባሰ ኤርትራውያኑ ወደ ሌላ ሀገራት ማምራታቸው የማይቀር ይሆናል።

ደቡብ ሱዳን

የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ምርት ወደ አለም አቀፍ ገበያ የሚቀርበው ሱዳንን አቋርጦ ነው። ደቡብ ሱዳን በየቀኑ ከ170ሺ በላይ በርሚል ድፍድፍ ነዳጅ በፖርትሱዳን በኩል ለአለም ገበያ ታቀርባለች። ከ800ሺ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በሱዳን ተጠልለው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በሱዳን የተፈጠረው ቀውስ የነዳጅ አቅርቦቷን እና ዋነኛ የገቢ ምንጯ እንዳይደናቀፍ በመስጋት ደቡብ ሱዳን ሁኔታውን በአይነቁራኛ በመከታተል ላይ ትገኛለች። በተጨማሪም በሱዳን ተጠልለው የሚገኙ ደቡብ ሱዳናውያን በተፈጠረው ቀውስ ሳቢያ ወደ ደቡብ ሱዳን ከተመለሱ ትልቅ ጫና እንደሚሆንባት በማመን አስጨምቋታል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.