ዜና፡ የሰላም ጥረቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች የሚደረገው ድጋፍ እና መፍትሔ እንዲጠናከር የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ጠየቀ

© UNHCR/Samuel Otieno

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2/ 2015 ዓ.ም፡– በኢትዮጵያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የበለጠ እንደሚያጠናክር ሃላፊው ፍሊፖ ግራንዴ አስታወቁ። በኢትዮጵያ በድርቅ እና የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተፈናቀሉም ሆኑ ስደተኞችን ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማስቻል ኮሚሽኑ ጥረቱን እንደሚያጠናክር ገለጸዋል።

ሃላፊው ይህንን ያስታወቁት በኢትዮጵያ ሲያካሂዱት የነበረውን የሶስት ቀን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋ በሰጡት መግለጫ ነው።

“ያለፉት ጥቂት አመታት ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ውስጥ ለነበሩ ሰዎች እጅግ አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም ሰላም ለማስፈን የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው፣ በጦርነቱ ሳቢያ ሁሉንም ነገር ያጡ ወገኖችን ለመርዳት እና ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በቦታው በመገኘት ለመመስከር ብቀቻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

የሰላም ስምምነቱ ከተደረሰ ጥቅምት ወር ጀምሮ ዩኤንኤችሲአር ከተባባሪ ድርጅቶች ጋር በመሆን በርካታ እገዛወችን ማድረጉን አስታውቋል። የህይወት አድን እርዳታዎች በተለይም ደግሞ መድሃኒት፣ የመጠለያ ቁሳቁሶቸ፣ አልባሳት፣ የቤት ቁሳቁሶቸ እና ብርድ ልብሶችን ማድረሱን አመላክቷል።

የአርዳታ አቅርቦቱ መሬት ላይ የሚታይ ሆኗል፤ ህዝቡ ድጋፍ እያገኘ ነው፤ አንዳንዶች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ሲሉ የገለጹት ኮሚሽነሩ በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ የሚደረገውን የመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ጥረትን ይበልጥ ማገዝ ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም ኮሚሽነሩ ይህ ተግባር በፈቃዳቸው ወደ ቀያቸው የሚመለሱትን ጨምሮ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እና ኑሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችል ወሳኝ ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል።  

ኮሚሽነሩ ከጎንደር በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው አለምዋሽ የስደተኞች ካምፕ የሰፈሩ ሃያ ሁለት ሺ የኤርትራ ስደተኞችንም የጎበኙ ሲሆን በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮነን  እና ሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መገናኘታቸው ተገልጿል።

ኢትዮጵያ እንደሁልጊዜው ስደተኞችን በማስጠለል ለምታደርገው ጥረትም ምስጋና አቅርበዋል። በርካታ ሀገራት ግጭት እና የተፈጥሮ መዛባት በሚገጥማቸው ሰዓት በራቸውን መዝጋት ይመርጣሉ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ግን አሁንም ከሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን የሚመጡ ስደተኞችን በመልካም መንገድ በመቀበል ላይ ይገኛሉ ሲሉ አወድሰዋል። አሰ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.