ዜና፡ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊነት የሚያደናቅፉና ከሱዳን ግዛት በመነሳት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሚሞክሩ አካላትን ሱዳን እንደማትታገስ ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/2015 ዓ.ም፡- የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊነት የሚያደናቅፉ እንደዚሁም ከሱዳን ግዛት በመነሳት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሚሞክሩ አካላትን ሱዳን እንደማትታገስ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ገለፁ፡፡

ሁለቱ አገራት በህዳሴ ግድብና በድንበር ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ልዩነትም በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና ህገወጥ የሰዎች፣ የጦር መሳሪያ እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር በጋራ ለመከላከልም ተስማምተዋል፡፡

ይህ የገለፀው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ጋር ትላንት ህዳር 22/2015 ካርቱም ውስጥ በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ባደረጉበት ወቅት መሆንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትብብር እንዲጎለብት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተቀራርበው ለመስራት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አክሎ ገልጧል።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሃት መካከል የሰላም ስምምነት በመፈረሙ መደሰታቸውን ገልፀው አገራቸው ለስምምነቱ አፈፃፀም ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

ከድንበር ጋር በተያያዘም የሚፈጠሩ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የሚደረግ ሙከራ ዘላቂ መፍትሄን የማያመጣ በመሆኑ ቀደም ሲል ሁለቱ አገሮች በፈረሟቸው ስምምነቶች አማካኝነት በሁለትዮሽ መስመር ለመፍታት ከመግባባት ተደርሷል ነው የተባለው።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል እየታየ ያለ በጎ የትብብር መንፈስ ልዩነቱን በሦስትዮሽ መንገድ ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት አዎንታዊ አሰተዋጽኦ እንዳለውም ጀኔራል አልቡርሀን ገልፀዋል።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ ደመቀ በድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ህገወጥ የሰዎች፣ የጦር መሳሪያ እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር በጋራ ለመከላከልም ተስማምተዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.