ዜና፡ ካርቱም ሚገኙት የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር በመኖሪያ ቤታቸው ጥቃት ደረሰባቸው፤ የአሜሪካ ኤምባሲ ተሽከርካሪው በጥይት መደብደቡ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10/ 2015 ዓ.ም፡- በጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የአገሪቱ መከላከያ ሀይል እና በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሀይል መካከል ከቅዳሜ እለት ጀምሮ በተከሰተው አለመረጋጋት በሱዳን መዲና ካርቱም ሚገኙት የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር በመኖሪያ ቤታቸው ጥቃት እንደተፈፀመባቸው የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት ጆሴፕ ቦሬል አስታወቁ፡፡

ጆሴፍ ቦሬል ጥቃጥ የደረሰባቸውን አምባሳደር ማንነት ባይገልፁም ነገር  ግን ደህና መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ጥቃቱ  የ ቪይና ኮንቬንሽን ስምምነትን በእጅጉ የጣሰ ነው  ያሉት ቦሬል የዲፕሎማቲክ ቦታዎችን እና ሰራተኞችን ደህንነት ማስጠበቅ የሱዳን ባለስልጣናት ቀዳሚ ኃላፊነት መሆኑንም በትዊተር ገፃቸው  ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ካርቱም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ተሽከርካሪው በጥይት መደብደቡን የዩኤስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ገልፀዋል። ተሸከርካሪው በ 100 ጥይቶች የተደበደበ ሲሆን በውስጡ ያሉት ግን ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ብሊንከንን ዋቢ በማድረግ አልአረቢያ ዘግቧል፡፡

በጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የአገሪቱ መከላከያ ሀይል እና በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሀይል መካከል ከቅዳሜ እለት ጀምሮ በተከሰተው ግጭት እስካሁን ከ 180 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና ከ1800 በላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ የሱዳን ቀውስ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ጥሪ ካደረጉ ሀገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ትላንት በሰጡት መግለጫ የሱዳን ሕዝብ አሁን ካጋጠመው ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለው ጥበብና ችሎታ ያለው ሕዝብ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ጠ/ሚሩ በአርብኛ በሰጡት መግለጫቸው የሱዳን ህዝብ የራሱን ችግር በራሱ የመፍታት ታላቅ ዓቅም እና ጥበብ ያለው ታላቅ ህዝብ በመሆኑ ማንኛውም የሁከት ዓላማን ያነገበ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያስተናግድ አይሆንም ብለዋል።

የሱዳን ህዝብ የራሱን ችግር በራሱ እንዲፈታ መተው ያለበት ሲሆን የማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነት ዓላማም ሰላምን እና ድርድርን በተመለከተ ብቻ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም ኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር አሊ ኤል ሳዲግ አሊ ጋር በስልክ መወያየታቸውን አስታውቀዋል፡፡   

በውይይታቸውም አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ለሱዳን ሕዝብ ያላትን አጋርነት እንዲሁም በተከሰተው ግጭት በሞቱ ዜጎች የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ የተከሰተውን ግጭት በማርገብ ወደ ቀድመ ሰላም እንደሚመለስ ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን በፌሽቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.