አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24/2015 ዓ.ም፡- በሁለቱ ጀነራሎች ሳቢያ በሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት ህዝቦቿን ለከፋ ሁኔታ እየዳረገ መሆኑን ግጭቱን አስመልክቶ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ዘገባወች እያመላከቱ ይገኛል። ህይወታቸውን ለማትረፍ የሚጥሩ ሱዳናውያን ቀያቸውን ትተው ስደትን ዋነኛ አማራጫቸው ማድረጋቸውም በመገለጽ ላይ ይገኛል።
የተባበሩት ምንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት እንዳስታወቀው የሱዳን ቀውስ ቶሎ መፍትሄ ካላገኘ በቀጣይ ከ800ሺ በላይ ሱዳናውያን ለስደት እንደሚዳረጉ ግምቱን አስቀምጧል። ለስደት ይዳረጋሉ ከተባሉት የሱዳን ነዋሪዎች መካከልም በየሀገሮቻቸው የተፈጠሩ ቀውሶችን በመሸሽ በሱዳን ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞችም ይገኙበታል።
የድርጅቱ ከፍተኛ ኮሚሽነር ራውፍ ማዙ በጀኔቫ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት ባቀረቡት ገለጻ እንደተናገሩት 815ሺ የሚሆኑ የሱዳን ነዋሪዎች ወደ ሰባቱ አጎራባች ሀገራት ሊሰደዱ እንደሚችሉ ከአጋሮቻችን ጋር ያደረግነው ምክክር አመላክቷል ብለዋል። ከዚህ አሃዝ ውስጥ 580ሺ የሚደርሱት ሱዳናውያን ሊሆኑ እንደሚችሉ እና ቀሪዎቹ 235ሺ የሚሆኑት ደግሞ ቀያቸውን ትተው በሱዳን ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። እንደ ድርጅቱ ይፋዊ መረጃ ከሆነ እስካሁን ከ73ሺ በላይ ሱዳናውያን ለስደት ተዳርገዋል። (ዘገባውን ከአልጀዚራ አገኘነው)