ዜና፡ ከታጣቂ ሀይሎች ጋር የሰላም ድርድር ሰለማይኖር ቡድኑን የተቀላቀሉ ወጣቶች እንዲመለሱ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አሳሰበ፤ ኢዜማ በበኩሉ መንግስት መዋቅሩን እንዲያፀዳ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/ 2015 ዓ.ም፡- የኦሮሚያ ክልል መንግስት በክልሉ ጸጥታን ለማረጋገጥ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንና  “የሼኔ አሸባሪ  ሃይልን” ወደ ሰላማዊ መንገድ ለማምጣት በርካታ ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም ኃይሉ እርስ በርሱ የማይደማመጥና ያልተደራጀ በመሆኑ መንግሥት ወደ እርቅ ድርድር መግባት እንደማይቻል አስታወቀ።

የክልሉ ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ህዳር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት  መንግስት ለየትኛውም አካል የሰላም እጁን የዘረጋ በመሆኑ በርካታ የሸኔ አባላት ለአባ ገዳዎች ፣ ለሀይማኖት አባቶች እና ለሀገር ሽማግሌዎች እጃቸውን እየሰጡ ነው።

የሰላም አማራጭን በመርገጥ ሀገርን ማሸበር በሚፈልግ ሃይል ላይ መንግስት ህግ የማስከበር ተግባር  እንደሚከተል ያስታወቁት አቶ ሃይሉ በስህተት ወደ ሸኔ ቡድን የተቀላቀሉ ወጣቶች ወደ ሰላም አማራጭ  እንዲመለሱ በአባገዳዎች፣ በሃገር ሽማግሌዎችና በህብረተሰ  ተሳትፎ  ጥረት ሲደረግ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

መንግስት ለሰላም የዘረጋውን እጁ ስለማይመልስ የታጠቁ ሃይሎች በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ ያስተላለፉት ሃላፊው ህብረተሰቡ ከክልሉ መንግስትና ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንዲሰራ አሳስበዋል።

ሃላፊው አያይዘውም የክልሉ መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በአማፂያኑ ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ሸኔ) የአለም አቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በበኩላቸው ለቪኦኤ እንደተናገሩት መንግስት ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ስለማይፈልግ አዲስ ፕሮፖጋንዳ ቢዘረጋም  የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የተደራጀ መዋቅርና አመራ  ያለው መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

መንግስት ከሸኔ ጋር በሽብርተኝነት የተፈረጀ  ህወሃት ጋር ያደረገውን  የሳለም ስምምነት ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር ለማድረግ ባለመፈለ የፈጠረው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ በኦነግ-ሸኔ የሽብር ቡድን የደፈጣ ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን፤ ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸውን፤ መታገታቸውን እና በሀገር ሀብት ላይ ውድመት እና ዝርፊያም መፈፀሙን ባሰባሰብኩት መረጃ ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ  ግድያ፣ የጅምላ ፍጅት እና ዝርፊያ እየፈጸመ ሰላማዊ ዜጎችን ሲያሰቃይ በመንግሥት በኩል የተወሰደው የመፍትሔ እርምጃ ግን የችግሩን ጥልቀት እና ውስብስብነት ከግምት ያስገባ አለመሆኑን ገልፅዋል፡፡

 “የዜጎችን ደኅንነት ማስከበር ያልተቻለው ሽብርተኞችን የሚያቅፍ እና የሚደግፍ መዋቅር መንግስት ውስጥ በመኖሩ ነው” ብሏል፡፡

ሸኔ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ግለሰቦችም ጭምር እንደሚደገፍ የጠቆመው መግለጫው  መንግሥት ጠንካራ እርምጃ ባለመወሰዱ የሰላማዊ ዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ እየተመሰቃቀለ እንደሚገኝ ኢዜማ ገልጧል፡፡

የሸኔ ቡድን ከጥቂት ዓመታት በፊት በተወሰኑ ዞኖች ብቻ ይንቀሳቀስ እንደነበር ያስታወሰው የኢዜማ መግለጫ በአሁኑ ወቅት በተለይ በኦሮሚያ ክልል በብዙ ቦታዎች ጥቃት ለማድረስ በሚያስችል ደረጃ ላይ ይገኛል ብሏል፡፡

ኢዜማ አያይዞም መንግሥት በመጀመሪያ በጉያው ውስጥ የተሰገሰጉትን የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎችን በማጽዳት ቁርጠኛ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.