በምህረት ገ/ክርስቶስ @MercyG_kirstos
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2015 ዓ.ም፡- “የሰላም ስምምነቱ ቢደረግም የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት አልተቀረፈም” ሲሉ የትግራይ ክልል ትልቁ የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ዶክተሮች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
ከጦርነቱ በፊት በፌደራል መንግስት ሲተዳደር የነበረው የዓይደር ሪፈራል የሆስፒታል ዶክተሮች ህይወት እድን የሆኑ የመድሃኒት ቁሳቁስ ድጋፍ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ክብሮም ገ/ስላሴ ተናግረዋል።
“ከሰላም ስምምነት በኋላም ምንም የተቀየረ ነገር የለም፣ የፌደራል መንግስት የላብራቶሪ ኬሚካል ግብእት (ሪጀንቶችን) ጨምሮ በጣም አስፈላጊ የሆኑት መድኃኒቶች ለሆስፒታሉ እያቀረበ አይደለም” ብለዋል ዶክተር ክብሮም።
ዶክተሩ እንደ ቀይ መስቀል እና አለማቀፍ የምግብ ፕሮግራም ያሉ የእርዳታ ድርጅቶች እያቀረቡ ያሉት የመድኃኒት ቁሳቁስ እርዳታ እጅግ ጥቂት መሆኑን ጠቅሰው ሆስፒታሉ የመንግስት ተቋም እንደመሆኑ በፌደራል መንግስት ሊደገፍ ይገባል ብለዋል።
ሆስፒታሉ ሰኞ እለት በትዊተር ገጹ የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ሌሎች ድርጅቶች የመድኃኒት እርዳታ እንዲያደርጉለት ተማጽኗል።
“በህክምና ውስጥ ከ60-70 በመቶ አስፈላጊ ውሳኔዎች፣ የላብራቶሪ መረጃን እንደሚያካትቱ ይታወቃል። ከጦርነቱ በኋላ ከሁለት ዓመት በላይ የዓይደር ሆስፒታል የላብራቶሪ የኬሚካል ግብእት (ሪጀንቶች) አላገኘም” ብሏል።
እንደ ዶ/ር ክብሮም ገለፃ ሆስፒታሉ በመቐለ ቅርንጫፍ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል አቅርቦት ኤጀንሲን የመድሃኒት ቁሳቁስ ቢጠይቅም ምንም አይነት ቁሳቁስ ከፌደራል መንግስት እንዳልተላከ ነው ምላሽ የሰጠው።
በጥቅምት ወር ዶ/ር ክብሮም ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ሆስፒታሉ በመድሃኒት፤ የላብራቶሪ ኬሚካሎች እጥረት እንዲሁም አዲስ አበባ ብቻ ሊጠገን የሚችለው የተበላሸ የሆስፒታሉ ማሽን፣ መጠገን ባለመቻሉ ሙሉ ለሙሉ እገልግሎት መስጠት የማይችልበት ደረጃ ደርሶ እንደነበር ገልፀው ነበር።
እንደ ካንሰር፣ አንቲባዮቲኮች እና የላብራቶሪ ሪጀንቶች ያሉ አስፈላጊ መድሃኒቶች እጥረት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን ሆስፒታሉ በጦርነቱ ወቅት ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት የፌደራል መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ዶክተሩ።
የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በታህሳስ ወር ባወጣው የሂደት ሪፖርት እንዳስታወቀው በትግራይ ክልል መቐለ የተለያዩ አካባቢዎች አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶች እና የህክምና አቅርቦቶች እነደተከፋፈለ ገልጾ ነበር።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ፀረ ወባ መድኃኒቶች፣ የስኳር በሽታ ሕክምና ኢንሱሊን፣ የኩላሊት እጥበት መድኃኒቶች፣ የቲቢ መድኃኒቶች፣ የደም ግፊት መከላከያ፣ የቤተሰብ ምጣኔ ሸቀጣ ሸቀጦችን ጨምሮ ሌሎች ነፍስ አድን መድኃኒቶች በዓለም ጤና ድርጅት እና የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኩል ተልኳል።
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ 158.3 ሜትሪክ ቶን አስፈላጊ መድሃኒቶች እና የህክምና አቅርቦቶች ወደ መቐለ እና በአቅራቢያው በሚገኙ የጤና ተቋማት በአለም አቀፍ እና በተመድ አጋሮች የተላኩ ሲሆን ተጨማሪ አቅርቦቶች በኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካል አቅርቦት አገልግሎት ተዘጋጅተዋል ብሏል። አስ