አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 9/ 2015፡- የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ(ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሱትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያቆሙ ጠየቁ፡፡
ድርጅቶቹ በኦሮሚያ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በክልሉ በመንግስት ኃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) መካከል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ተደጋጋሚና ዘግናኝ ግድያዎች ቀጥለዋል ሲል ገልፀዋል፡፡
“የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አሰሳ” በሚል ከነሃሴ 1/2015 ዓም እስከ ነሃሴ 4/2015 እያደረጉ በቆዩት ዘመቻ፤በምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦ፣ ጮቢ፣ ዳኖ፣ ግንደበረት፣ ኢልፈታ፣ ኢሉገላን፣ ሊበን ጃዊ እና ሚዳ-ቀኚ ወረዳዎች ምንም የማያውቁ አርሷደሮች ላይ ግድያ፣ ተኩሶ ማቁሰል፣ እስር እና ዘረፋ በመንግሰት ኃይሎች ተካሄዷል ብለዋል።
በተለይም በሰላማዊ ህዝብ ላይ ቂም መወጣት በሚመስል መልኩ ነሃሴ 4/2015 ዓ.ም በጮቢ ወረዳ በኬ ሆፉ በሚባል ቀበሌ 11 ሰላማዊ ሰዎች በመንግስት ኃይሎች ዘግናኝ በመሆነ መንገድ ተገድለዋል ሲል ኦፌኮ በመግለጫው ገልጧል።
ኦፌኮ የሟቾቹን ስም የዘረዘረ ሲሆን ከነዚህም መሃል፤ አቶ ከረዩ አራርሳ እና ወ/ሮ አራርሴ (ባልና ሚስት)፤አቶ ጉርሙ ጂፋራ፤አቶ ተስፋዬ ጂፋራ እና ወጣት አበራ ጂፋራ (የአንድ ቤተሰብ ወንድማማች የሆኑ)፤አቶ ፊጣ ሚልኬሳ እና አቶ ሞጎራ ሚልኬሳ(ወንደማማቾች)፤ አዛውንት ዱጋሳ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ጡሩ ያዴሳ የተባሉ ሰዎች ሁሉም በየቤቶቻቸው ሳሉ እየተዞረ የተገደሉ መሆናቸውን ገልፆ፣ ወጣት ቶሎሳ ዲሪባ እና አቶ ግርማ በከራ ወደ ስራ ለመሰማራት በመንገድ ላይ በመገኘታቸው በጭካኔ በጥይት ተደብድበው የተገደሉ መሆናቸውን አስታውቋል።
ከዚህም ውጪ በዛኑ በጮቢ ወረዳ የተፈጸው ጅምላ ግድያ ጾታና እድሜ ያልለየ ነው ያለው ድርጅቱ በተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች መካከል ታዳጊ ወጣቶች፣ የ70 አመት አዛውንት፣ ወላድ እናትና የ11 ዓመት ህጻናት ይገኙበታል ብሏል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) በበኩሉ ሙሉ ኦሮሚያ ክልል ሊባል በሚችል ደረጃ በተለይ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ይንቀሳቀስበታል በሚባል አካባቢ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው የጅምላ ግድያ እና ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲል ገልጧል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው በማዕከላዊ ኦሮሚያ ምዕራብ ሸገር ኦኖታ አምቦ፣ ዳቦ፣ ኢሉ ገላን፣ ሊበን ጃዊ፣ ሚዳ ቀኝ፣ ፋታ፣ ጮቢና ግንደበረትበቅደም ተከተል ነሀሴ 7፣ 8፣ 10 እና 11 2023 ዓ.ም ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የጅምላ እስር፣ ጥቃት፣ ዝረፋና የጅምላ ግድያ በመንግስት ሀይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈፅሟል ሲል አስታውቋል፡፡
ነሃሴ 7 2023 ጌዶ ከተማና ባቢቻ ከተማ እና ሃሮ መረሚ ወረዳ ጉዲሳ ነገዎ የተባሉ ግለሰብ እና ልጆቹን ጨምሮ ስድስት ቤተሰቡ፣ የወረዳው ከ30 በላይ ነዋሪዎች በማሰር ንብረታቸው በሙሉ ተዘርፈዋል ሲል ከሷል፡፡
ነሃሴ 8 ቀን የ60 አመት እድሜ ባለፀጋ የሆኑትን አቶ ጉዲሳ ነጋው ከታሰሩበት ባቢቻ ከተማ እስር ቤት በማስወጣት በጥይት ገድለዋቸዋል ያለው የኦነግ መግለጫ በኬ ሆፉ ወረዳ ልዩ ቦታው ሺመላ በሚባል አካባቢ አስራ አንድ ሰዎችን በጥይት ገድለው አምስት ሰዎችን ደግሞ አቁስለው ጥለው ሄደዋል ብሏል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ(ኦፌኮ) እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ጥቃቶችን ለመቅረፍ ተጀምሮ የነበረውን የሰላም ውይይት አንዲቀጥል የመከረ ሲሆን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) በበኩሉ የኦሮሚያ ክልል የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጥሪ አቅርቧል፡፡አስ