ዜና፡ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በስድስት ከተሞች የባጃጅ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ጥሎት የነበረው ክልከላ አነሳ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 9/ 2015 ዓ.ም፡- የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሸዋ ሮቢትና ላሊበላ ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪዎች እንዳይንቀሳቁ ጥሎት የነበረውን ክልከላ ማንሳቱን አስታወቀ፡፡

ዕዙ በከተሞቹ የባጃጅ ተሸከርካሪዎች እስከ ነሐሴ 17፣2015 ድረስ እንዳይንቀሳቀሱ ያደረገውን ክልከለ በመሻር ከነገ ነሐሴ 10 ቀን 2015፣ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ፈቅዷል፡፡

ከዚህም ጋር በማያያዝ ክልከላዉ ከተነሣበት ጊዜ ጀምሮ የባጃጅ ባለቤቶችና አሽካርካሪዎች “የጽንፈኛ ቡድን” ሲል የጠራቸው አባላት፣ የዘረፉትን ንብረቶችና የትኛዉንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ከማጓጓዝ እንዲቆጠቡና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥብቅ ትዕዛዝ መስጠቱን ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ አስታውቋል፡፡ ይህንን ተላልፈዉ በተገኙት ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማሕቀፍ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድም አዟል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ የፈጠረለትን ሰላማዊ ሁኔታ በመጠቀም አርሶ አደሩ ወደ መኸር አዝመራ ሥራዉ እየተመለሰ ነው ያለው የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ የግብርና ግብአቶችንም ወደ የአካባቢዎቹ ለማጓጓዝ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ዕዙ በግምገማው መገንዘቡን ገልጧል፡፡ በቀጣዮቹ ቀናት በሚወሰዱ የማጥራት እርምጃዎች የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥብቅ መመሪያ መስጠቱም ተገልጧል፡፡

የሁለተኛዉ ዙር ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሥራዎች ከሞላ ጎደል እየተጠናቀቁ ነው ያለው ዕዙ ሕዝቡ ለመከላከያ ሠራዊታችን እያሳየ ያለው አቀባበል፣ የስንቅና የማበረታቻ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን፣ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ ያለው ፍላጎትና እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን አመላክቷል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.