ዜና፡ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አንድም አቃሎት የሚያውቀው ችግር የለም፣ በትግራይ የተካሄደው አስከፊው ጦርነት የቆመው በፖለቲካ ውይይት ነው – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው 

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 9/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ነሃሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁ ይታወቃል። ምክር ቤቱ በዝግ እንዳካሄደው በተገለጸው ስብሰባ ወቅት የምክር ቤቱ አባል ከሆኑት መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የአማራ ክልል ፕሬዝደንት አቶ አንዳርጋቸው የሰጡት አስተያየት ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለሀገሪቱ ችግሮች ዋነኛ መፍትሔ ማበጃ መንገዱ ፖለቲካዊ ውይይት እና ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት ብቻ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጆች አንድም ያቃለሉት ችግር የለም፣ በትግራይ የተካሄደው አስከፊው ጦርነት የቆመው በፖለቲካ ውይይት ነው ብለዋል።

በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ከፍተኛ እልቂት መፈጸሙን በንግግራቸው ያስታወቁት አቶ ገዱ ከብዙ እልቂት በኋላ፣ ከብዙ የጋራ ጥፋት በኋላ ፖለቲካዊ ውይይት ሲጀመር ያ ጥፋት ወደ መገታቱ ሄደ ሲሉ ገልጸዋል።

ፖለቲካዊ ችግሮችን በጠመንጃ ሀይል መፍታት ቢቻል ኑሮ ኢትዮጵያ በምድር ላይ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ትሆን ነበር ሲሉ የተደመጡት አቶ ገዱ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በሀይል ለመፍታት በርካታ አስቸኳይ ግዜ አዋጆች ታውጀው መተግበራቸውን አውስተው ቁጥር ስፈር የሌላቸው ወታደራዊ ኮማንድ ፖስቶች በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በተለያዩ ግዜ ተቋቁመው ቢንቀሳቀሱም አንድም ያቃለሉት ችግር የለም ብለዋል። በኢትዮጵያ የተወሰነ የሰላም ፍንጭ የታየው በፖለቲካዊ መንገድ ለመፍታት በተሞከረባቸው አከባቢዎች ብቻ ነው በማለት የትግራዩን ጦርነት በአብነት ጠቅሰዋል።

በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ እና በምክር ቤቱ አባላት በተደጋጋሚ ንግግራቸው እንዲቋረጥ የተደረጉት አቶ ገዱ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ቀውስ ዋነኛ ምክንያት ብለው ያቀረቡት እሳቸው ወክለው የተወዳደሩለት የብልጽግና ፓርቲን ነበር። አቶ ገዱ በንግግራቸው ለአማራ ክልል መሰረታዊ ችግር ዋነኛ ምክንያቱ የብልጽግና መንግስት የፖለቲካ ውድቀት ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ወክለው ተወዳድረው እንዲያሸንፍ ያደረጉትን የብልጽግና መንግስት በንግግራቸው በተደጋጋሚ የተቹት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የብልጽግና መንግስት አሁንም ካለፉት አምስት አመታት ጥፋቶቻችን መማር አለመቻሉ ይገርመኛል ብለዋል። ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ራሱ ፖለቲካዊ ችግር ይፈጥራል፤ ችግሩን በፖለቲካዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት ይንቀሳቀሳል ይህ አሁን ያለው መንግስት ባህሪ ሁኗል ሲሉ መንግስታቸውነ ገልጸውታል።

የአማራ ህዝብ ከምር ተቆጥቷል፣ የተቆጣን ህዝብ ደግሞ በሀይል በወታደራዊ መንገድ ማሸነፍ አይቻልም ያሉት አቶ ገዱ የአማራ ክልልን ችግር ለመፍታት ወታደራዊ መንገድ ከመጠቀም ይልቅ ፖለቲካዊ ውይይት ነው የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ንግግራቸው በምክር ቤቱ አባላት የአካሄድ ጥያቄ እና አስቸኳይ ስብሰባውን በመሩት ምክትል አፈጉባኤዋ ከመቋረጡ በፊት በምክረ ሀሳብነት ካቀረቧቸው ሀሳቦች መካከል አንደኛው መከላከያ ሰራዊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ካምፑ ይመለስ ያሉበት ይገኛል። አቶ ገዱ ስለመከላከያ የአማራ ክልል እንቅስቃሴ ሲገልጹም ድሮውንም ወደ ማይመለከተው ስራ እንዲገባ ተደርጎ በእጅጉ ያከብረው ከነበረው ህዝብ ጋር እንዲጋጭ መደረጉ ስህተት ነው ያሉ ሲሆን መንግስት በራሱ ክፋት እና አቅመ ቢስነት ያጣውን ቅቡልነት በመሳሪያ ሀይል ለማስመለስ በሚያደርገው ጥረት መከላከያን እየተጠቀመበት ነው ሲሉ አመላክተዋል።

በሁለተኝነት ያቀረቡት ምክረ ሀሳብ ደግሞ የአማራ ህዝበ እና የብልጽግና ፓርቲ ግንኙነት በማይጠገንበት ደረጃ ስለተበጠሰ በአስቸኳይ ሁሉንም የአማራ ሀይሎች ያቀፈ ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ችግሩን ለማቃለል መሞከር የሚለው ይገኝበታል። ሶስተኛ ምክረ ሀሳባቸውን በአማራ ላይ የሚደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጥቃት የተቃወሙ የሚሉ ቃላትን ተጠቅመው ሀሳባቸውን ሳይጨርሱ እንዲያቋርጡ ተደርገዋል።

በመጨረሻም ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ባስተላለፉት መልዕክት የምክር ቤቱ አባላት ይህንን አዋጅ ማጽደቅ የለባቸውም ሲሉ ተናግረዋል። የግዜ ጉዳይ ካልሆነ ሁሉም በየተራ የሚደርሰው ይሆናል ብለዋል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁነው ከማገልገላቸው ባለፈ እሰከ ቅርብ ግዜያት ድረስ በመንግስት ተመድበው ሲሰሩ እንደነበር የሚታወቀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪነት ሚናቸው ነው። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.