አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 13/ 2015 ዓ.ም፡- በስደተኞች ጉዳይ ላይ በመስራት የሚታወቀው “እኛለኛ በስደት” የተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የሚያበረክተውን የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ቀን ሽልማት በዛሬው እለት ነሃሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ተሸለመ፡፡
ለድርጅቱ በዛሬው ቀን ለሚከበረው የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ቀንን (World Humanitarian Day) በማስመልከት በቤሩት ከተማ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሽልማት የተበረከተለት በመካከለኛው ምስራቅ ከአፍሪካና ከእስያ ለመጡ የሰው ቤት ሰራተኛ ሴቶች ላበረከተው የሰብዓዊ እርዳታ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባዘጋጀው የሽልማት ስነ ስርዓት ላይ የእኛለኛ በስደት ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሪት ጽጌሬዳ ብርሃኑ እና በአመራሩ አባላት የሆኑት ወ/ሪት ማስረሻ ግርማ እና ወ/ሪት መሰረት ማንደፍሮ ተገኝተው ሽልማቱን ተቀብለዋል ተብሏል።
ችግርን ለመሸሽ ወደ ሊባኖስ ተሰድደው በሰው ቤት ሰራተኝነት ተሰማርተው የነበሩት እና አሁን ላይ የድርጅቱ ኃላፊዎች የሆኑት ወ/ሪት ማስረሻ፣ ወ/ሪት ጽጌሬዳ እና ወ/ሪት መሰረት፤ “ሽልማቱ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በተለያዩ ችግሮች ያለፉት እና ከተጠቂ ማህበረሰቦች የተወጣጡ ሴቶችን በአመራር ቦታ በመመደብ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችል ያሳያል” ብለዋል።
ኃላፊዎቹ ለተበረከተላቸው ሽልማት ምስጋናቸውን አቅርበው ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ለተወጣጡ የሰው ቤት ሰራተኞች መብት በሚታገሉበት ወቅት ላለፉት 6 ዓመታት ከጎናቸው የነበሩትን ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በስፍራው ተገኝተው የነበሩት የሊባኖስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ሳደህ አል ሻሚ እና በሊባኖስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ ጉዳዮች ሃላፊ ኢምራን ሪዛ ከእኛለኛ በስደት አባላት ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውም በመግለጫው ተገልጧል፡፡
ለእኛለኛ በስደት የተሰጠው የዘንድሮ ሽልማት ለኢትዮጵያዊ ድርጅት ሲሰጥ የመጀመርያው ሳይሆን እንዳልቀር ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
የእኛለኛ በስደት ግብረ ሰናይ ተቋም ሊባኖስ ላይ በኢትዮጵያውያን የሰው ቤት ሰራተኛ ሴቶች በ2009 ዓ.ም ተቋቁሞ የሚመራ ሲሆን ላለፉት 6 ዓመታት በሊባኖስ ላሉት የሰው ቤት ሰራተኞች እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ ለሚመለሱ ስደተኞች ሲያገለግል ቆይቷል።
ተቋሙ በስደት ላይ ላሉት የሰው ቤት ሰራተኞች ጥብቅና የሚቆም በጎ አድራጎት ድርጅት ነው። ድርጅቱ ሊባኖስ ላሉትና በብዙ እንግልት የሚያልፉ ለሰው ቤት ሰራተኞችን የሰብዓዊ እርዳታ በማበርከት እስር ቤት ለታሰሩት ጠበቃ በመቅጠር እና ወደ ኢትዮጵያ የመመለሻ ትኬት እና ሌሎች ወጪዎች በመሸፈን ላለፉት ስድስት ዓመታት ስደተኛ እህቶችን ሲያገለግል ቆይቷል።
የእኛለኛ በስደት ተቋም ከ2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ምዝገባው ተጠናቅቆ ቢሮ ከፍቶ ከመካከለኛው ምስራቅ ለተመለሱት ሴቶች የተለያየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በመስራት ላይ ይገኛል።
ይህ ግብረ ሰናይ ድርጅት በሊባኖስ በስደት ላይ ካሉት የቤት ሰራተኞች መካከል 68 ከመቶ ለጾታዊ ትንኮሳ መዳረጋቸውን ሊባኖስ ከሚገኘው የሊባኖስ አሜሪካን ዪኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ባዘጋጀዉ ጥናት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ አስ