ዜና፡ ኢዜማ የደቡብ ከልል ም/ቤት አና የፓረቲው አባል አቶ ታረቀኝ ደግፌ በውል ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን አስታወቀ

አቶ ታረቀኝ ደግፌ : ፎቶ፡ ማህበራዊ ድህረ-ገፅ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19/ 2015 ዓ.ም፡- በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ኢዜማን ወክለው ተመርጠው የደቡብ ከልል ም/ቤት አባል ሆነው በማገልገል ላይ ያሉት አቶ ታረቀኝ ደግፌ ህዳር 17 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በውል ወደማይታወቅ ቦታ መወሰዳቸውን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡

አቶ ታረቀኝ የክልል ምክር ቤት አባል መሆናቸው እየታወቀ ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን ባላነሳበት ሁኔታ ህግን በመተላለፍ  ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን ፓርቲው በማህበራዊ ትስስር ገፁ ገልጧል፡፡

የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ህገ መንግስት አንቀፅ 49 (2) (ለ) ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል ከባድ ወንጀል ሲፈፅም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፍቃድ አይያዝም ፤ በወንጀል አይከሰስም በሚል በግልፅ የተደነገገ መሆኑን ያስታወሰው ፓርቴኢው የተፈፀመውን ድርጊት አውግዟል፡፡ 

ኢዜማ አያይዞም የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ገልፆ ማንኛውም ነገር  ህግና ህግን ብቻ መሰረት ተደርጎ ሊከናወን እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተን ለማሳሰብ እንወዳለን ብሏል፡፡

ፓርቲው አባሎቹ ላይ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በመንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝም አሳውቋል፡፡

የጉራጌ ዞን የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ተከትሎ ኢ-መደበኛ ቡድኖች አየፈጠሩ ያሉት ሁከትና ብጥብጥ በመደበኛ ህግ ማስከበር ስርዓት ማስቆም ባለመቻሉ ከህዳር 16 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ በተደራጀ ኮማንድ ፖስት እንዲመራ መወሰኑን የደቡብ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ መግለፁ ይታወቃል፡፡

የቢሮዉ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በተደረገ ፀጥታን የማስከበር እንቅስቃሴ በጥፋቱ የተሳተፉ ያሉዋቸው ከ 70 ባላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልፀው ነበር።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.