አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3/2015 ዓ.ም፡- በ2022 ኢትዮጵያ በተፈናቃዮች ብዛት ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን በማስቀደም በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የኖርዌ የስደተኞች ካውንስል የተፈናቃዮች ክትትል ማዕከል አስታወቀ፡፡ ማዕከሉ ይፋ ያደረገው የ2022 አመታዊ መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ አጠቃላይ ተፈናቃዮች ቁጥር ሁለት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ አምስት ሺ መሆኑን አስታውቋል። ከዚህ ውስጥ ሁለት ሚሊዮን 32 ሺ የሚሆኑት የተፈናቀሉት በግጭት እና ብጥብጥ ምክኒያት መሆኑም ተገልጧል፡፡
እንደ ማዕከሉ ሪፖርት ከሆነ የፈረንጆቹ 2022 አመት በአለም አቀፍ ደረጃ 71.1 ሚሊየን ህዝብ በግጭት እና በተፈጥሮ ሳቢያ የተፈናቀለበት አመት ሁኖ ተመዝግቧል፡፡
በኢትዮጵያ በድርቅ ሳቢያ ብቻ በ2022 ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 686ሺ መሆኑን የጠቆመው ማዕከሉ በተለይም በኦሮምያ እና ሶማሌ ክልሎች ሁኔታው የከፋ መሆኑን አስታውቋል፤ በሁለቱ ክልሎች ከድርቁ በተጨማሪ ግጭት እና ሁከት ጉዳት እንዳደረሰባቸው አመላክቷል።
በአለማችን በ2022 ከቀያቸው ከተፈናቀሉ ህዝቦች መካከል ሶስት አራተኛው የተፈናቀለው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአስር ሀገራት መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል። ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 31 ነጥብ 7 ሚሊየን መሆኑን መረጃው አስታውቋል።
በተጨማሪም በ2022 በከፍተኛ ሁኔታ የምግብ ስጋት ካጋጠማቸው አምስት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን የማዕከሉ ሪፖርት ያሳያል፤ ናይጀሪያ፣ አፍጋኒስታን፣ የመን እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሌሎቹ በማዕከሉ የተጠቀሱ ሀገራት ናቸው።
በኢትዮጵያ በ2021 የነበረው ተፈናቃይ ቁጥር ከአምስት ሚሊየን በላይ መሆኑን ያወሳው ሪፖርቱ በትግራይ የነበረው ጦርነት ዋነኛ ምክንያት እንደነበር ገልጿል።በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የተደረሰው ስምምነት በተፈናቃዮች ዘንድ ዘላቂ ሰላም ይሰፍናል የሚል ተስፋ እንዳጫረባቸው ያመላከተው ሪፖርቱ የሰላም ስምምነት ቢፈረምም የሰሜኑን የሀገሪቱን ክፍል ሙሉ በሙሉ ለማረጋጋት አመታትን እንደሚፈጅ አመላክቷል።