አዲስ አበባ፣ጳጉሜ 1፣ 2014 ዓ.ም፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ስር በሚገኘው ኡሙሩ ወረዳ ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በታጣቂ ኃይሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ነዋሪዎች የተገደሉ፣ የቆሰሉ እና ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ወደ ኦቦራ ከተማ መፈናቀላቸው በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳስብ መሆኑን ገለጸ። ኮሚሽኑ ጥቃቶቹን ተከተሎ ነዋሪዎችን እና የመንግሥት አካላትን አነጋግሯል።
ኮሚሽኑ እንደገለለፀው በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ፣ በኡሙሩ ወረዳ በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል ያለ ሲሆን አክሎም በነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ቀበሌ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ የሚጠራ) ታጣቂዎች የወረዳው ዋና ከተማ የሆነችውን ኦቦራ ከተማን ለመያዝ ባደረጉት እንቅስቃሴ ሦስት የአማራ ብሔር ተወላጆች መግደላቸውን ተከትሎ ከኡሙሩ ወረዳ፣ ሀሮ አዲስ ዓለም ከተባለ ቀበሌ እና አጎራባች ከሚገኘው የአማራ ክልል፣ ቡሬ ወረዳ የተውጣጡ ታጣቂዎች በኡሙሩ ወረዳ በሚገኙና አገምሳ፣ ጆግ ምግር፣ ታም ኢላሙ፣ ጀቦ ዶባን፣ ጦምቤ ዳነጋበ፣ ጃዋጅ፣ ኛሬ፣ ለገ ሚቻ፣ ሉቁማ ዋሌ በሚባሉ ቀበሌዎች የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ነዋሪዎች ላይ ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጥቃት ፈጽመዋል ሲል በመግለጫው አትቷል ።
ኢሰመኮ “በእነዚህ ሁለት ቀናት በተደረጉ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፤ ከ70 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን፣ የነዋሪዎች የቤት ንብረቶች እና የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸውን ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች ለመረዳት ችሏል” ብሏል፡፡
መግለጫው ጥቃት ከተፈጸመባቸው ቀበሌዎች መካከል አሁንም ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን እና በጥቃቱ ምክንያትም ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በኦቦራ ከተማ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በተጨማሪም በጥቃቶቹ ምክንያት የተፈጠረው የደኅንነት ስጋት ያልተቀረፈ መሆኑን እና በዞኑ ውስጥ ካሉት ወረዳዎች መካከል በጃርደጋ ጃርቴ፣ ኪረሙ እና በአቤ ዶንጎሮ ወረዳዎች ተመሳሳይ ጥቃቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ስጋቶች መኖራቸውን ኮሚሽኑ ከነዋሪዎች ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያሳያሉ ሲልም አክሏል፡፡
ኮሚሽኑ ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንዲሰማሩ እና ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ ነዋሪዎችን ወደ ተረጋጋ ሕይወት የመመለስና ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ እንዲሠራ አሳስቧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ክትትል ማድረጉን የሚቀጥል መሆኑንና በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመው አሳዛኝ ጥቃት ያሳሰበው መሆኑን ገልጸው በማንኛውም ጊዜ የፀጥታ ስጋት ካለባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ ቦታ በሚዘዋወሩበት ወቅት የነዋሪዎች በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት እና የንብረት መብቶች ለአደጋ እንዳይጋለጡ ተገቢ የሆኑ ጥንቃቄዎች ሊደረጉ እንደሚገባ በድጋሚ አስታውሰዋል። አስ