ዜና፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መንግሥት ያልተገደበ የኃይል አጠቃቀም እንዲተገብር የሚያመቻች እንዳይሆን ሲል ኢዜማ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 2/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአማራ ክልል ከታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ጋር የተያያዘ መግለጫ አውጥቷል። ኢዜማ ባወጣው መግለጫ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመንግሥት ያልተገደበ የኃይል አጠቃቀም እንዲተገብር የሚያመቻች እንዳይሆን ሲል አሳስቧል። በተጨማሪም አዋጁንም ተገን በማድረግ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ሲል አስጠንቅቋል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅታዊ መረጋጋት እንጂ ዘላቂ ሀገራዊ ሠላምን የሚያመጣ መንገድ ሰላልሆነ መንግሥት በአማራ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ውይይት እና ሰላማዊ መፍትሔን በማስቀደም ችግሩን ለመፍታት በሙሉ ልብ እንዲሠራ ሲል አሳስቧል።

የታጠቁ ኃይሎችም ለሚቀርቡ የሠላም ጥሪዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ከግጭት የሚጎዳውን ንፁህ ዜጋ በመታደግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

በመላ ሀገሪቱ በተለይም በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ለተፈጠረው አለመረጋጋት ገዢው ፓርቲ ብልጽግናን ተጠያቂ ያደረገው ኢዜማ የሰላም እጦቱና አለመረጋጋት ምንጩ በጠራ የፖለቲካ መስመር ላይ መቆም ያልቻለው፤ አቋምም ሆነ አቅም የሌለው የብልፅግና አመራር ነው ብሏል። የቀውሶቹ መሠረታዊ ምክንያት በብልፅግና ውስጥ ያለው የጋራ ርዕይ መጥፋት፤ ዛሬም ከመንደርተኝት ያልወጡ እበላ ባይ ካድሬዎች የእርስ በእርስ መጓተትና መካረር ብሎም በተለይ በየክልሉ እርስ በእርስ በመጓተት ላይ ያሉ ካድሬዎች የሚመሩት የመንግሥት የአስተዳደር ድክመት እና በደል እንደኾነ በጥብቅ ሊታወቅ ይገባል ሲል ገልጿል።

መንግሥት ሃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ ካለመወጣት የመነጩ ተቃውሞዎች ሲነሱበት ነው አስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚያውጀው ሲል ተችቷል። የሰላም መደፍረሶችን እና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ለመፍታት በሚል እሳቤ በተደጋጋሚ ሀገራዊ እና ክልላዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ተግባራዊ ሲደረጉ ታዝበናል ያለው የኢዜማ መግለጫ መንግሥት እነዚህን አስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ተገን በማድረግ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ይበልጡኑ የተቃውሞ መጋጋሚያ ምክንያት ሲሆኑ መመልከት የተለመደ ነው ብሏል።

በዚህ ወቅት በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭትም ድንገት የተከሰተ ሳይኾን መንግሥት ሃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ ባለመወጣቱ የተከማቹ ሀገራዊ የፖለቲካ ትኩሳቶች የግለታቸው ጫፍ ላይ ሲደርሱ የተፈጠረ ነው ሲል በምክንያትነት አስቀምጧል። ይህ ለዓመታት የታመቀው ብሶት፣ የመጠቃት ስሜት እና ተስፋ መቁረጥ ገደፉን አልፎ ክልሉን አሁን ላለበት ሁኔታ ዳርጎታል ብሏል።

ከዚህ ቀደም ለነበሩ በደሎች ቅሬታዎች እና ስጋቶች ተገቢውን መልስ በትክክለኛው ሰዓት አለመሰጠት እና አሁንም ከስጋት ነፃ የሆነ ድባብ አለመፈጠሩ ውጥረቱን አባብሶ አሁን ላለበት ውጥንቅጥ እንዳበቃውም ጠቁሟል።

መንግሥት በአማራ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ከማርገብ ጎን ለጎን መዋቅራዊ የኾነ ሀገር አቀፍ የዘላቂ ሰላም መላ እንዲቀይስ የጠየቀው ኢዜማ መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን አቅጣጫዎች አስቀምጧል።

በመፍትሔነት ካስቀመጣቸው መካከልም ክልሉን ለዚህ ደረጃ እንዲበቃ ያደረገው መንግስት ሃላፊነቱን ካለመወጣቱ የመነጨ መሆኑን ተገንዝቦ ለእያንዳንዶቹ ጉዳዮች በግልጽ እራሱን ተጠያቂ በማድረግ ማህበረሰቡን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚለው ይገኝበታል። መንግሥት የሚዘውራቸው የህዝብ መገናኛ ብዙሃን፣ ፋና እና ዋልታ ሚዲያዎች መንግሥት በጉዳዩ ላይ አንዳች ነገር ሲተነፍስ ብቻ ተቀብለው የገደል ማሚቱ ከመሆን ባለፈ የችግሩን ምንጭን ከመሰረቱ በማሳየት በደሎች ተዳፍነው እንዳይቀሩ የመስራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲል ጠይቋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.