ዜና፡ በክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ መደፍረስ ችግር በውይይትና በድርድር ለመፍታት ተከታታይ ጥረቶች እንደሚደረጉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 2/ 2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል ያጋጠመውን የጸጥታ መደፍረስ ችግር በውይይትና በድርድር ለመፍታት ተከታታይ ጥረቶች እንደሚደረጉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎት መስሪ ቤቱ ትላንት ለመንግስት ሚዲያዎች ባሰራጨው መግለጫ በአማራ ክልል ያጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ ችግር አሁንም በውይይትና በድርድር የሚፈታበት መንገድ ዝግ ባለመሆኑ ተከታታይ ጥረቶች እንደሚደረጉ ገልጾ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የጸጥታ መደፍረስ እንቅስቃሴ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡

አገልግሎቱ “ከድርድርና ውይይት ይልቅ መንግሥታዊ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚጥሩ እንዲሁም አጋጣሚዎችን በማቀነባበር ዝርፊያ ለመፈጸም የሚፈልጉ የታጠቁ ቡድኖች፣ ፅንፈኛና አክራሪ ኃይሎች” ያላቸው አካላት፣ ከውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ሀገራዊ የጸጥታ ሥጋት ለመደቀን ሙከራ እያደረጉ ነው ሲል  ገልጧል፡፡ ሰሞኑን በአማራ ክልል እየታየ ያለው ሁኔታም ለዚህ አብነት መሆኑን ጠቁሟል፡፡

“ቀደም ሲል ከኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል የተከሰቱ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት፣ከሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር ተከታታይ ጥረቶች ቢደረጉም ችግሩ በሚፈለገው መንገድ አልተፈታም” ያለው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መግለጫ፤ ለዘረፋ የተደራጁ ጥቂት ኃይሎች አሁን ላይ መንግሥታዊ መዋቅሮች እንዲፈርሱ፤የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት እንዲቋርጡ፤ አንዳንድ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚያገናኙ የመንገድ መሠረት ልማቶች እንዲዘጉ በማድረግ፤ ሕዝቡ ላይ ማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ ብሏል።

ለዝርፊያ ከተደራጁ ቡድኖች ጋር የሚንቀሳቀሱ አካላት ካሉ በሚጠናቀሩ መረጃዎችና ማስረጃዎች አማካኝነት አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድባቸውና ሕግ የማስከበር ሂደቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን የሚያስፈፅመው የጠቅላይ መምሪያ ዕዝን በማስተባበር የክልሉን ሰላምና ደኅንነትን በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ የሚያግዝ ስምሪት ወስዶ እየሠራ መሆኑን አመልክቷል፡፡

መግለጫው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ እነዚህ ለዘረፋ የተደራጁ ኃይሎች ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ለሀገር ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ጉልህ አስተዋጽዖ ሲያበረክት የኖረውን የአማራን ሕዝብ ታሪክ ለማጠልሸት ሞክረዋል ሲል ከሷል፡፡

መላው የክልሉ ነዋሪዎች ግን መንግሥት እያደረገ ያለውን ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ በመደገፍ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ እየጣሩ ነው ያለው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መግለጫ፤ ይህንንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.