ዜና፡ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆም ስምምነት ላይ መደረሱን በመልካም ተቀበሉት፣ ስምምነቱ በአፋጣኝ እንዲተገበር ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25/ 2015 ዓ.ም፡- የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት እና የተለያዩ ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና በሕወሓት ተወካዮች መካከል በደቡብ አፍሪካ የግጭት ማቆም ስምምነት መፈራረማቸውን በደስታ ተቀብለውታል፡፡

በአፍሪካ ህብረት መሪነት ከጥቅምት 25 ጀምሮ በፕሪቶሪያ ሲካሔድ የነበረው የሰላም ድርድር ሲጠናቀቅ ተፋላሚዎቹ ወገኖች ግጭቱን ለማቆም ረቡዕ ተስማምተዋል፡፡

የህብረቱን መግለጫ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ በሰጡት መግለጫ ‹ስምምነቱ ኢትዮጵያን ከአራት ዓመት ተኩል በፊት የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ ወደፊት ለማራመድ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው› ብለዋል፡፡ ‹ለሰላም ያለን ቁርጠኝነት የፀና ነው፡ እናም ለስምምነቱ ትግበራ የመተባበር ቁርጠኝነታችንም በተመሳሳይ መልኩ ጠንካራ ነው› ሲሉም አክለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ቡድን አሸማጋዮች፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለደቡብ አፍሪካ መንግስት እና ‹ለኢትዮጵያ ወዳጆች› በአጠቃላይ ምስጋናቸውን የገለፁ ሲሆን፣ በተንታኞች እምነት በሰላም ድርደር ሂደቱ ላይ አሜሪካ ያላትን ሚና ግን አላነሱም፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ባለስልጣናት የግጭት መቋጫ ስምምነት መፈራረማቸውን እንደሚያመሰግኑ ተናግረዋል፡፡ አክለውም የአፍሪካ ህብረት ‹ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላም እና ዕርቅ ለመፍጠር ለፓርቲዎቹ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዕርግጠኛ ነው› ብለዋል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ጦርነቱን ለማቆም መፈራረማቸውን በተመለከተ አሜሪካ ‹እርምጃውን በደስታ እንደምትቀበለው› ተናግረዋል፡፡

‹ግጭትን በማቆም፣ ችግሮችን ለመፍታት ውይይተን በማስቀጠል፣ ሰላምን ለማጠናከር እና ሁለት አመታት የሚጠጋውን ግጭት ለማስቆም ተስማምተው ይህንን የመነሻ እርምጃ የወሰዱ አካላትን እናደንቃለን፡፡ ለዚህ ስምምነት ተግባራዊነት የሚገባውን የሰብዓዊ እርዳታ እና የንፁሃን ዜጎች ጥበቃን እንቀበላለን› ብለዋልም፡፡

ስምምነቱን ለማሳካት የአፍሪካ ህብረት ላደረገው ‹አስገራሚ ጥረት› አመስግነው ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ለአፍሪካ ህብረት ምስጋናቸውን የገለፁበትን መግለጫ በደስታ እንደሚቀበሉና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሚኖሩ እና በጦርነቱ ለተጎዱ ለህሉም ማህበረሰቦች መልሶ ግንባታና ልማትን ለመደገፍ ላሳዩት ቁርጠኝነት አጋርነታችንን እንገልፃለን› ሲሉ አክለዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል ስምምነቱን የተፈራረሙ ሁለቱንም ወገኖች እንኳን ደስ አላችሁ እያሉ ‹በስምምነቱ መሰረት ፈጣን ትግበራ› እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.