አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 12/ 2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሽሬ፣ አላማጣና ኮረም ከተሞች ያሉ የባንኩን ቅርንጫፎች ከፍቶ ደምበኞች ገንዘብ ማስቀመጥ እንዲሁም ከሃገር ዉስጥ እና ከውጭም ጭምር የሚላክላቸው ገንዘብ መቀበል ያሚያስችላቸዉን አገልግሎት መጀመሩን አስታዉቋል።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረዉ አለመረጋጋት ምክንያት በትግራይ ክልል ሲሰጥ የነበረዉን የባንክ አገልግሎት ለማቋረጥ መገደዱ ያስታወቀው ባንኩ “በቅርቡ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሽሬ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተማዎች በሚገኙ ቅርንጫፎቻችን ከውጭ ሀገር እና ከሀገር ውስጥ የሚላኩ ገንዘቦችን የመቀበል እንዲሁም ገንዘብ የማስቀመጥ አገልግሎት መስጠት የተጀመረ መሆኑን በደስታ ለማሳወቅ እንወዳለን” ሲል በማህበራዊ ትስስር ገፁ ያስታወቀ ቢሆንም ገንዘብ የገቢ ማድረግ እና ወጪ የማድረግ አገልግሎትን ግን አልጀመረም፡፡
በዚህም አሰራር ደንበኞች ገንዘብ ገቢ ማድረግ እንዲሁም የተላከላቸዉን መቀበል እንደሚችሉ አስታውቋል። ሆኖም ነዋሪዎች አሁንም የቀድሞ ቁጠባቸውን ማግኘት አይችሉም።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽሬ ቅርንጫፍ የመከፈቱን ዜና እንደሰሙ ወዲያው ከአካውንታቸዉ ገንዘብ ለማውጣት ወደ ቅርንጫፉ ሄደው የነበረ ቢሆንም፤ ገንዘብ ስለሌለ ምንም አይነት ገንዘብ ሊሰጣቸው እንደማይችል ተነግሯቸው እንደተመለሱ ተናግረዋል።
“ሰዎች ባንኩ በመከፈቱ ደስተኛ ሆነው ነበር ነገር ግን ገንዘባቸውን ማግኘት እንደማይችሉ ሲሰሙ ተስፋ በመቁረጥ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል” ብለዋል።
የባንኩን መከፈት እንደሰሙ በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ባንኩ ያሄዱ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው “ሰራተኞቹ ባንኩን ክፈቱ ስለተባሉ ብቻ ነው የከፈቱት እንጂ ምንም ገንዘብ እንደሌለ ነግረውኛል። የተላከልኝ ገንዘብ ካለ ብቻ የተወሰነ መጠን ከ2,000 እስከ 3,000 ብር ሊሰጠኝ እንደሚችል ነገሩኝ” በማለት አክለዋል።
ባንኩ ደምበኞች ለምን የቀደመ ቁጠባቸውን ማግኘት እንደማይችሉ የገለፀው ነገር ባይኖርም በቀጣይ ሁኔታዎች እንደፈቀዱ አገልግሎት በጀመሩ ቅርንጫፎች አገልግሎቱን በማስፋትና በየደረጃው በሁሉም ቅርንጫፎች አገልግሎት ለማስጀመር ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል። አስ