አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21/ 2015 ዓ.ም፡- በፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰብ መብት ላይ የሚደረጉ ገደቦች እና በአባላቶቻቸው ላይ የሚደርሱ እንግልቶች በዘላቂነት ሊቆሙ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡
ኮሚሽኑ ዛሬ መጋቢት 21 ቀን ባወጣው መግለጫ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ በእናት ፓርቲ እና በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የመሰብሰብ መብት መከልከል እንዲሁም የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ምሥረታን ተከትሎ በፓርቲው አስተባባሪዎች ላይ ስለደረሰው እንግልትና እስራት መከታተሉን ገልጧል፡፡
በክትትሉም መሰረት እናት ፓርቲ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በሚገኘው አዳራሽ ሊያካሂደው የነበረው የፓርቲው ጠቅላላ ስብሰባ እንዲሁም ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በጋምቤላ ሆቴል ውስጥ ሊያካሂድ የነበረው የፓርቲው ጠቅላላ ስብሰባ እንዳይካሄድ መስተጓጎሉን አረጋግጫለው ብሏል፡፡
አክሎም ለፓርቲዎቹ ስብሰባ ተዘጋጅተው የነበሩ ቦታዎች ጥበቃዎችና ሠራተኞች ማንነቱ ተለይቶ ካልታወቀ የበላይ አካል ተሰጥቷል ባሉት ትዕዛዝ መሠረት ስብሰባዎቹን መከልከላቸው እና ስብሰባዎቹ ሊካሄድባቸው በነበሩበት አካባቢዎች የደንብ ልብስ በለበሱ የፖሊስ አባላት እና ሲቪል ልብስ በለበሱ የጸጥታና ደኅንነት አባላት ስብሰባው እንዲካሄድ ከማገዝና ከማሳለጥ ይልቅ የማደናቀፍ ተግባር መከናወኑን አመላክቷል፡፡
የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ምሥረታን ተከትሎ የፓርቲ አስተባባሪዎች ላይ እስራት እና እንግልት የተፈጸመ መሆኑንም ተገንዝቢያለሁ ብሏል፡፡
ኢሰመኮ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ክትትሎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፖለቲካ ፓርቲ እና የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በተለይም የአመራር አባሎች ላይ ገደብ፣ ማዋከብ እና እስራት መከናወኑን አስታውሷል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔዎቻቸውንም ሆነ ሌሎች የድርጅቶቻቸውን ስብሰባዎች እንዳያደርጉ የሚደረጉ ወከባዎች፣ ክልከላዎችና እገዳዎች የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና የመሳተፍ መብቶች ጥሰቶች ናቸው ያለው ኮሚሽኑ መንግሥት ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ክልከላዎችን በመጠቀም ዜጎች የመሰብሰብ መብታቸውን ከመጠቀም እንዲያፈገፍጉ ከማድረግ መቆጠብ አለበት ብሏል፡፡
መንግስት በመሰብሰብ መብት ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ ተግባሮችን የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እንዲሁም ዜጎች የመሰብሰብ መብታቸውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የማመቻቸት እና ለተሳታፊዎች ጥበቃ እና ከለላ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ኢሰመኮ በመግለጫው አመላክቷል።
የመሰብሰብ መብት በተለይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና አስፈላጊ በመሆኑ ዜጎች የመሰብሰብ መብታቸውን እውን ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ መንግሥት ሕጋዊ ቅቡልነት ባላቸው ምክንያቶች፣ አስፈላጊነት እና ተመጣጣኝነት ቅድመ ሁኔታዎችን ያላሟሉ፣ ድንገተኛ እና ከታሰበላቸው ዓላማ በላይ የሆኑ እርምጃዎችን ከመውሰድ የመቆጠብ ግዴታ አለበት ሲል አሳስቧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰብ መብት እና የሰዎችን በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ መብታቸውን የሚገድቡ ተግባሮችን የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት የመንግሥት ነው” ብለዋል፡፡አስ