ፍኖተሰላም ከተማ ፤ ፎቶ – የከተማው ኮሚኒኬሽን ፌስቡክ ገፅ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 9/ 2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተሰላም ከተማ የአየር ድብደባ ሊሆን ይችላል በተባለ ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎች ሲሞቱ ከ 55 ባለይ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሶባቸው በከተማው በሚገኝ ፍኖተሰላም አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምና ላይ መሆናቸውን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ፡፡
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ የሆኑት ማናዬ ጤናው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ጥቃቱ የተፈፀመው እሁድ ነሃሴ 7 ቀን 2015 ዳሞት በሚባል ሆቴል አጠገብ ነው፡፡ “ጠዋት ላይ ከባድ የፍንዳታ ድምፅ ተሰማን ከዚያ ወዲያውኑ በርካታ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሆስፒታሉ መምጣት ጀመሩ” ሲሉ የገለፁት ኃላፊው ሁሉ ተጎጂዎቹ ወንዶች መሆናቸውን ጠቅሰው እድሜያቸው በ20ዎቹ ውስጥ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የከተማው ነዋሪ ጥቃቱ ጠዋት ወደ 4 ሰዓት መፈፀሙን ገልፆ የጥቃቱ ሰላባ የሆኑት ሰዎች በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት በከባድ ተሸከርካሪ ወደ ማንኩሳ ለመጓዝ በዝግጅት ላይ ነበሩ ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድቷል፡፡ ነዋሪው በተሽከርካሪው ውስጥም ሆነ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በጥቃቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል።
ነዋሪ አክሎም “ ጥቃቱ የደረሰው በሰው አልባ አውሮፕላን ሳይሆን እንዳልቀሰ ጠቅሶ ምናልባትም ቦምብ ወይም ሌላ ከባድ መሳሪያ ሊሆን እንደሚችልም ተናግሯል።
የፍኖተሰላም አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ማናዬ ጤናው ለሁለት ሳምንታት ያህል በዘለቀው የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጥ ሳቢያ የህክም አቅርቦቶችና የኦክስጂን እጥረት መከሰቱን ገልፀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰዎች እየሞቱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ስራ አስኪያጁ ተጨማሪ ሞት እንዳይከሰት የትራንስፖርት አገልግሎትን ወደነበረበት በመመለስ እና አስፈላጊ የሆኑ የህክምና አቅርቦቶች ለማድረስ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ለሚመለከታቸው አካላት ተማፅነዋል። አስ