አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12 /2015 ዓ.ም፡- በተደጋጋሚ በሚከሰተው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ምክኒያት መንግስት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞኖች በተለይም በአራቱ የወለጋ ዞኖች የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ማከናወን አለመቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽማሊስ አብዲሳ በትላንትናው እለት በነቀምት ከተማ ከወለጋ ማህበረሰብ ጋር ባደረጉት የውይይት መድረክ ላይ ገለፁ፡፡
በአራቱ የወለጋ ዞኖች በጀት የተመደበላቸው የመንገድ፣ የኤልክትሪክ፣ የትምህርት ቤቶች እና የፋብሪካዎች ግንባታ በፀጥታ ምክኒያት መቋረጣቸውን ጠ/ሚሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በምስራቅ ወለጋ ብቻ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የብልፅግና ፓርቲ ሃላፊዎች መገደላቸውን ገልፀዋል፡፡
ከአስመራ ተመልሰው የትጥቅ ትግል እያካሄዱ ያሉት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ተዋጊዎች ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመለሱ ጥሪ አድርገዋል።
“ከእኛ በሃሳብ የሚለዪ ሰዎች ከዛሬ ጀምሮ መግባት ይችላሉ። ሁለተኛ ደግሞ በሰላም ገብተው ሃሳባቸውን መግለጽ ይችላሉ። ለምርጫ የቀረው ሦስት ዓመት ነው። አስተዋዩን የወለጋ ህዝብ በመልካም ሃሳብ ካሳመኑ ህዝቡ ሊመርጣቸው ይችላል። ነገር ግን በጉልበት መሆን የለበትም” ብሏል።
ወለጋ ባለው የፀጥታ ችግር መንግስት በእጅግ መቸገሩን የገለፁት አብይ አህመድ ህብረተሰቡ የአካባቢዉን መሰረተ ልማት በመጠበቅ መንግስትን እንዲረዱ “የልማት ስራዎች እንዳይቋረጡ እርዱን” በማለት ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስቴሩ ከአንድ መቶ በላይ የመንግስት ኃላፊዎች በታጣቂ ሃይሎቹ መገደላቸውን በመግለፅ የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉት ሃይሎቹ የልማት ፕሮጄክቶችን በማውደም እና ንፁሃን ዜጎችን በመግደለ ከሷቸዋል፡፡
ከደምቢ ዶሎ ጋምቤላ ድረስ ተጀምሮ የነበረው የምንገድ ስራ በፀጥታ ችግር ምክኒያት መቋረጡን ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ገልፀዋል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በተደጋጋሚ ወደ ሰላማዊ ትግል እንደሚገባ ቢገልፅም የፌድራሉ መንግስት በተጨባጭ የወሰደው እርምጃ የለም፡፡ የኦነሰ ሃላፊዎች በበኩላቸው መንግስት እያደረገ ያለው የውይይት ጥሪ ታዓማኒነት ያለው አይደለም በማለት ሶስተኛ ወገንን ያካተተ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ገልፅ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ አስ