ዜና፡ በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከ50 በመቶ በታች ላመጡ ተማሪዎች የመቁረጫ ነጥብ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6/2015 ዓ.ም፡- በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከ50 በመቶ በታች ላመጡ ተማሪዎች የአቅም ማሻሻያ (Remedial Program) በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች እና በተለያዩ አማራጮች ለመከታተል የመቁረጫ ነጥብ ይፋ መደረጉን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር በ2014 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ አገር አቀፍ ፈተና ወስደው 50 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ያመጡትን ከግምት ውስጥ በማስገባት እና በተመሳሳይ ሁኔታ ፈተናው የተሰጠበትን አግባብ እና ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት በመውሰድ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል የአቅም ማሻሻያ (Remedial Program) እንዲተገበር መወሰኑ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት በሁሉም አማራጮች (በግል እና በመንግስት ተቋማት) የአቅም ማሻሻያ  (Remedial ፕሮግራም)  ለመከታተል ተማሪዎች እንደተፈተኑት የትምህርት አይነት ብዛት 30 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ማለትም (210 ከ 700፣ 180 ከ 600 እና 150 ከ 500) በመሆን የተቆረጠ መሆኑ ተገልጧል።

ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግስት ተቋማት (ወጪያቸው በመንግስት ተሸፍኖ) የ Remedial ፕሮግራም የሚከታተሉት ይፋ የሆነውን መቁረጫ ነጥብ ያሟሉ ብቻ ይሆናል ሲል ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት የተፈጥሮ ሳይንስ ወንድ ተማሪዎች ፤ ከ700 በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የረሜዲያል መቁረጫ ነጥብ  263 ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ሴት ተማሪዎች ፤ ከ700 በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የረሜዲያል መቁረጫ ነጥብ  227 ፣ የማህበራዊ ሳይንስ ወንድ ተማሪዎች ፤ ከ600 በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የረሜዲያል መቁረጫ ነጥብ  220 ፣ የማህበራዊ ሳይንስ ሴት ተማሪዎች ፤ ከ600 በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የረሜዲያል መቁረጫ ነጥብ  190 እንዲሆን ተወስኗል፡፡

እንዲሁም የታዳጊ ክልል የተፈጥሮ ሳይንስ ወንድ ተማሪዎች ፤ ከ700 በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የረሜዲያል መቁረጫ ነጥብ 210 ፣ የታዳጊ ክልል የተፈጥሮ ሳይንስ ሴት ተማሪዎች ፤ ከ700 በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የረሜዲያል መቁረጫ ነጥብ  210 ፣ የታዳጊ ክልል የማህበራዊ ሳይንስ ወንድ ተማሪዎች ፤ ከ600 በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የረሜዲያል መቁረጫ ነጥብ 180 እና የታዳጊ ክልል የማህበራዊ ሳይንስ ሴት ተማሪዎች ፤ ከ600 በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የረሜዲያል መቁረጫ ነጥብ  180 ሆኖ ተወስኗል፡፡

በተጨማሪም የአርብቶ አድር አካባቢ የተፈጥሮ ሳይንስ ወንድ ተማሪዎች ፤ ከ700 በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የረሜዲያል መቁረጫ ነጥብ 210፣ ለሴት 210 እንዲሁም የአርብቶ አድር አካባቢ የማህበራዊ ሳይንስ ወንድ ተማሪዎች ከ600 180 ለሴት 180 ሲሆን የአይነ ስውራን የተፈጥሮ ሳይንስ ወንድ ተማሪዎች ፤ ከ700 ለወንድ 210 ለሴት 210፣ የአይነ ስውራን የማህበራዊ ሳይንስ ወንድ ተማሪዎች  ከ500 ለወንድ 150 ለሴት 150 እንዲሆን ተወስኗል፡፡

በ2015 የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው የአቅም ማሻሻያ (በ Remedial ፕሮግራም) የሚከታተሉ ተማሪዎችን አነስተኛ የመግቢያ ውጤት መወሰን አስፈላጊ በመሆኑ 50 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ያላስመዘገቡ ነገር ግን ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን የሚያሟሉ ተማሪዎች የ Remedial ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ተብሏል።

የ2014 ዓ.ም የ12 ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከተፈተኑት አጠቃላይ 896 ሺ 520  ተማሪዎች ውስጥ 50 በመቶ እና በላይ ያመጡ ተፈታኞች 29,909 (3.3በመቶ) ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ጥር 19/ 2015 ዓ.ም መግለፁ ይታወቃል

የዘንድሮው ውጤት እጅግ አስደንጋጭ ነው ያሉት የትምህርት ሚንቴሩ ፐሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለዚህም ተጠያቂዎቹ  “መንግስት፣ ተማሪዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መምህራን እንዲሁም ወላጆች” መሆናቸውን ገልፀው በውጤቱ የወደቁት ተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ሀገሪቱ  የትምህርት ስርዓትም መውደቁን ያሳያል ብለዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.