አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22/2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል በተነሳው ጦርነት በሴቶች እና በሕፃናት ላይ ለጦርነት ዓላማ ስልታዊ በሆነ መልኩ ጨምሮ መጠነ-ሰፊ ጥቃቶች መፈፀማቸውን እና በሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች በተለያየ ወቅት በተነሱ ግጭቶች ሴቶችና ሕፃናት ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መጋለጣቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ይህን ያለው ከመስከረም 2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ ትናንት ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት ሲሆን ሪፖርቱ በድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት እንዲሁም ኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ በሴቶችና ሕፃናት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩንም አክሎ ገልጧል፡፡
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በሀገሪቷ በተከሰቱት ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ሕፃናት ከመንግሥት፣ ከማኅበረሰብ እና ከቤተሰብ ማግኘት ያለባቸው ጥበቃ በመጓደሉ ለተደራራቢ የመብቶች ጥሰት መጋለጣቸው እና ሴቶች በተፈጸሙባቸው ጾታዊ መድሎዎችና ጥቃቶች ምክንያት መሰረታዊ መብቶቻቸውን የሚጥሱ፣ ነጻነቶቻቸውን የሚገድቡ እንዲሁም ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያጎድፉ በደሎች እንደደረሱባቸው ይፋ አድርጓል። በማከልም በብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥም ለሕፃናትና ለሴቶች ሰብአዊ መብቶች በቂ የሕግ ከለላ በመስጠት ረገድ የተለያዩ ክፍተቶች ተስተውለዋል ብሏል።
“ለተፈጸሙ ጥቃቶች ውጤታማ ፍትሕ እና መፍትሔ የሚያስገኝ የወንጀልና የፍትሐ-ብሔር የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር እና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያሟላ የወንጀል ምርመራና የክስ አመሰራረት መጓደል አሳሳቢ ጉዳዮች” ናቸው ሲል ገልጧል።
እንደ ኮሚሽኑ ሪፖሪት፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ሕፃናት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው፣ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥም ለጾታዊ ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጋላጭ መሆናቸውና ልዩ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረጉ የሰብአዊ ድጋፎች አለማግኘታቸው ተደራራቢ የመብቶች ጥሰትን አስከትሏል።
በሀገሪቱ በተከሰቱ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት ሳቢያ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶች በመቋረጣቸው፣ ወይም የተለያዩ ገደቦች መኖራቸው በሴቶችና ሕፃናት ትምህርትና ጤና የማግኘት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። ሴቶችና ሕፃናት ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ለብዝበዛ መጋለጥ፣ በኢንደስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች መሰረታዊ መብቶች ጥሰቶች መቀጠል እና በእነዚህ የመብቶች ጥሰት ረገድ የቁጥጥርና የተጠያቂነት መላላት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ሪፖርቱ እስታውቋል።
የኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ “ሰብአዊ መብቶችን ማክበር፣ ማስጠበቅ እና ማሟላት የመንግሥት ዋነኛ ግዴታ በመሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን፣ ተቋማትን እና አሠራሮችን በማሻሻል፣ ፍትሕን ተደራሽ በማድረግ፣ በግጭቶች የወደሙ የትምህርትና የጤና ተቋማትን እና ሌሎች መሰረተ-ልማቶችን መልሶ በመገንባት እና ለተጎጂዎች ሁለንተናዊ ተሐድሶን በማመቻቸት የሕፃናትንና የሴቶችን ሰብአዊ መብቶች የማሻሻል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት” ብለዋል። አስ