አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የብሉናይል ግዛት ኩርሙክ ከተማ በሱዳን ጦር ሰራዊት እና በአከባቢው በሚንቀሳቀሰው የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ ሰሜን በተሰኘ አማጺ ቡድን መካከል ትላንት ንጋት ላይ ውጊያ መካሄዱን ምንጮቹን ዋቡ በማድረግ ሮይተርስ የዜና ወኪል አስታወቀ።
በብሉ ናይል ግዛት የተነሳውን ውጊያ የሸሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአከባቢው ነዋሪዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁን ዘገባው አካቷል።
በጉዳዩ ዙሪያ ሱዳን ፖስት ይዞት በወጣው ዘገባ ግጭቱ የተጀመረው በሱዳን ከሚንቀሳቀሱ አማጺ ቡድኖች ውስጥ ትልቁ እንደሆነ የሚነገረው የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ ሰሜን በሱዳን ጦር ሰራዊት ካምፕ ላይ ጥቃት በመፈጸሙ መሆኑን አመላክቷል።
በሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች ግጭት ሳቢያ ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከ52ሺ በላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁ ይታወሳል። አስ