አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6/ 2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ ከ22 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ በኢትዮጵያ 22 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በጥናት መለየቱን ገልጸው ድጋፉ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሰሜኑ ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በነበረው ጦርነት ጉዳት በደረሰባቸው የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የሚኖሩ 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች የእለት ደራሽ ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው የገለፁት ዳይሬክተሩ ኮሚሽኑ ድጋፉን ተደራሽ የማድረጉ ተግባር መንግስት ከሌሎች 23 አጋር አካላት ጋር በመሆን ባልተገደበ ሁኔታ እያከናወነ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
አክለውም በኦሮሚያ ክልል በወለጋ አንዳንድ አካባቢዎች ያለውን ግጭት ተከትሎ ወደ 30 ሺ የሚጠጉ ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልፀው ለተፈናቃዮች የተላከው ድጋፍ ነቀምት ከተማ መድረሱን አስረድተዋል፡፡
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ከ400 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን በአካባቢው ላይ በቅርቡ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ ሰብዓዊ ድጋፉን ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ለማድረስ የጸጥታው ሁኔታ አዳጋች ያልሆነባቸውን አማራጮች በመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ዋልታ ዘግቧል፡፡
እነዚህን የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች የመለየቱ ስራ በዓመት ሁለት ጊዜ የመንግስታቱ ድርጅት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚያከናውኑት መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተው ለሰብዓዊ ድጋፍ 3 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ተመድቦ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል፡፡ አስ