ዜና፡ በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው የመንግስት ወኪሎች ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል ሲል ኢሰመኮ አሳሰበ፤ በርካታ ሰዎች የድርጊቱ ሰለባ መሆናቸውን አጋለጠ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 28/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች እየጨመረ የመጣውን የመንግስት ወኪሎች የአስገድዶ መሰወር ድርጊት እና ተይዘው የሚገኙበትን ሁኔታ አለማሳወቅ ተግባር በአፋጣኝ እንዲቆምና ይህንን ድርጊት ለመከላከል የተደነገገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ተቀብላ እንደታፀድቅ አሳሰበ፡፡

ኢሰመኮ አስገድዶ የመሰወር ድርጊት ላይ ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ ግንቦት 28፣ 2015 ይፋ ባደረገው መግለጫ ድርጊቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከመሆኑም በተጨማሪ በቤተሰብ ላይ የሥነ ልቡና ጉዳት እና ጭንቀት የሚያስከትልና ማኅበረሰቡ በሕግ ሥርዓት ላይ ያለውን እምነት የሚሸረሽር አደጋ ነው ሲል ገልጧል፡፡

አስገድዶ መሰወር አንድን ሰው የሚገኝበትን ቦታና ሁኔታ ሳይታወቅ “በመንግሥት ወኪሎች” በእስር መያዝ፣  በተለይ በከባድ ወንጀል ተጠርጥሯል የተባለን ሰው ለወንጀል ምርመራ በሚል ምክንያት ከቤተሰብ እና ከጠበቃ እንዳይገናኝ አድርጎ በእስር የማቆየትን ተግባር የሚገልጽ ፅንሰ ሐሳብ ነው ያለው ኮሚሽኑ እነዚህ ሁለቱም ድርጊቶች “ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች” መሆናቸውንና የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል በአሳሳቢ ሁኔታ መባባሱን አስታውቋል፡፡

ኢሰመኮ አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ የሲቪልና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታና ደኅንነት ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ስፍራ እየተወሰዱ  እንዲሰወሩ የተደረጉ ናቸው ብሏል፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ከተወሰኑ ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ወራት መሰወር በኃላ የተገኙ መሆናቸውን ገልጾ አሁንም በግዳጅ እንደተሰወሩ የቀጠሉ አሉ ሲል ገልጧል።

ከተጎጂዎች መካከል የተወሰኑት ሲያዙ በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ መሆኑ ተነግሯቸው ወደ መደበኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ የተሰወሩ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ምንም ሳይነገራቸው በጸጥታ ኃይሎች ተወስደው የተሰወሩ ናቸው ሲል ከሚሽኑ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ ከሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በማስገደድ ተሰውረው ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ከተለያየ የጊዜ መጠን መሰወር በኃላ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው የተገኙ ሲኖሩ፣ አስገድደው በተሰወሩበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ ገላን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የቀድሞው ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ ተይዘው እንደቆዩ ለመረዳት ተችሏል ብሏል መግለጫው።

በአማራ ክልል በባሕር ዳር እና በደብረ ብርሃን ከተማ የአስገድዶ መሰወር ሰለባዎች የሆኑ ሰዎች መካከል አንድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ከሠራዊቱ ከድቷል በሚል በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ወረብ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑትን ወላጅ አባቱን ልጅህን አምጣ በሚል ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በግዳጅ ተወስደው ተሰውረው ከቆዩ በኋላ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ተለቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አንድ የቀድሞ የሶማሊ ክልል ልዩ ኃይል አባል ታኅሣሥ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ከቢሮ ተደውሎለት ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሮ እንዲመጣ ተጠርቶ ከሄደ በኋላ በዕለቱ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጅምሮ ስልኩ የተዘጋ ሲሆን፣ ከዚያ ቀን ጀምሮ የት እና ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ አለመቻሉን ኢሰመኮ አመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ቢያንስ ሰባት ሰዎች የአስገድዶ መሰወር ድርጊት ሰለባ ከሆኑት መካከል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በወረዳው ፖሊስ ከሌሎች ሦስት ጓደኞቹ ጋር ተይዞ ፖሊስ ጣቢያ ከገባ በኋላ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሌሎቹ ታሳሪዎች ተለይቶ ነቀምት ከተማ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መዘዋወሩን ለቤተሰብ የተነገረ ቢሆንም ከዚያ ቀን ጀምሮ ያለበትን ቦታ እና ሁኔታ ማወቅ አልተቻለም ሲል አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የምሥራቅ ወለጋ ዞን የኦፌኮ አስተባባሪ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት በመንግሥት የደኅንነት ኃይሎች ተይዞ ነቀምት ከተማ በሚገኘው የጸጥታ ቢሮ ውስጥ ታስሮ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶበት እንደነበረና እጁ በሰንሰለት በመታሰሩ ምክንያት ከቤተሰብ የሚሄድለትን ምግብ ተቀብሎ መመገብ እንዳቃተውና ግለሰቡ ከጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሊገኝ አለመቻሉንም ኮሚሽኑ ገልጧል።

“የተወሰኑት መጀመሪያ ከተመዘገቡበት ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱት ከመደበኛው የተጠርጣሪ እና የእስረኛ የዝውውር ሂደት ውጪ እና በምሽት በመሆኑ ፍለጋቸውን አስቸጋሪ አድርጎታል” ያለው መግለጫው ቡራዩ ከተማ በተለምዶ አሸዋ ሜዳ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ  በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊሶች ተይዞ ከሁለት ወራት የፖሊስ ጣቢያ ቆይታ በኋላ ከሌሎች እስረኞች ተለይቶ  መወሰዱ የታወቀ ቢሆንም ፣ ከዚያን ቀን ጀምሮ ያለበትን ቦታ እና ሁኔታን ማወቅ አልተቻለም ብሏል፡፡

ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ ቁጥራቸው ከሃያ ያላነሱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሱሉልታ ወረዳ፣ ለገሄጦ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር፣ ልዩ ስሙ ረቡዕ ገበያ፣ 04  ቀበሌ አንድ ሰው ይዘው የሄዱ ሲሆን፤ በማግስቱ ቤተሰቦቹ ታሳሪውን ለመፈለግ ወታደሮቹ ይኖሩበት ወደነበረው ደርባ ቶኒ፣ አበባ ልማት ካምፕ ቢሄዱም፣ ወታደሮቹ የተያዘው ግለሰብ ያበትን ሁኔታ ሊያሳውቁ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን፤ ይልቁንም ለመጠየቅ የሄዱ ሰዎች እስር እና ማስፈራርያ የደረሰባቸው መሆኑና የተያዘው ግለሰብም እስከ አሁን ድረስ ያለበት ሁኔታ እና ቦታ ማወቅ አለመቻሉን ኢሰመኮ በመግለጫው አካቷል፡፡

የአስገድዶ መሰወር ድርጊት እጅግ አስከፊ የሆነ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን በግለሰቡና  በቤተሰቦቹ ላይ የሚያስከትል መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው ማናቸውም የወንጀል መከላከልና አጥፊዎችን የመቅጣት ሥራ ሙሉ በሙሉ በሕጋዊና ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ ሥርዓት ብቻ ሊመራ የሚገባው ነው ብሏል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ይህ አስከፊ የሆነ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም መንግሥት አስፈላጊውን ጊዜያዊ እና ዘለቄታዊ እርምጃዎች ሁሉ እንዲወስድ፣ የተሰወሩ ሰዎች ሁሉ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ፣ በተሰወሩበት ጊዜ ሁሉ የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ የተሟላ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ችግሩ የደረሰበትን አሳሳቢ ሁኔታ ከግምት በማስገባት  ሀገር አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ የሥራ ቡድን በማዋቀር የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማፈላለግ እና ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “መንግሥት የአስገድዶ መሰወር ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መፍትሔ መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን ወንጀል ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፤ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ተቀብላ እንድታጸድቅ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.