ዜና፡ በአዳማ ከተማ በፈነዳ ቦምብ የአንድ ሰው ሞት እና ሰባት ሰዎች መቁሰልን ተከትሎ ፖሊስ 11 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ

አዳማ ከተማ ፤ ፎቶ ማህበራዊ ድረ-ገፅ

በጌታሁን ለገሰ @Birmaduu2

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19/ 2015 ዓ.ም፡- በአዳማ ከተማ ትላንት ታህሳስ 18 ቀን ምሽት ላይ  በተፈፀም የቦምብ ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን እና ሌሎች ሰባት ሰዎች መቁሰላቸውን የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ሃትሪክ ጃምቦ ሃውስ በተባለ ባር ውስጥ ከምሽቱ 2 ሰአት ላይ ጥቃቱ መፈፀሙን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አባል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል። ጥቃቱን ተከትሎ ፖሊስ ዘጠኝ ወንዶችን እና ሁለት ሴቶችን በአጠቃላይ አስራ አንድ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስረዋል። 

እንደ ፖሊሱ ገለጻ ወንጀሉ በማን እንደተፈፀመ እና ከወንጀሉ ጀርባ ያሉ ምክንያቶችን ለማጣራት ተጨማሪ ምርመራ ይደረጋል። ምርመራው እንደተጠናቀቀም ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ኮሙኑኬሽን ቢሮ በፌስቡክ ገፁ ባወጣው አጭር መግለጫ በጥቃጡ አንድ ሰው መሞቱን ያረጋገጠ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ብዛት ግን ሶስት መሆናቸውን ነው የገለፀው፡፡ ጨምሮም የፀጥታ አካላት ተጠርጣሮዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያደረገ ይገኛል ብሏል፡፡

ህዳር 29 ቀን 2015 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ስፍራው ጎሮ አካባቢ ዊኬር በተባለ ግሮሰሪ ውስጥ በፈንዳ ቦንብ በሰባት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.