አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 1/ 2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት አሳስቦኛል ሲል የአለም ጤና ድርጅት ገለፀ፡፡
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በትዊተር ገፃቸው፣ በአማራ ክልል መንገዶች በመዘጋታቸው እንዲሁም ኢንተርኔት እንዲቋረጥ መደረጉ ለግኑኝነት አዳጋች ሁኔታ መፈጠሩና የሰብዓዊ እርዳታን ወደ ክልሉ ለማድረስ አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልፀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ግጭት በፍጥነት በሰዎች ጤና ላይ እና ዘለግ ላለ ጊዜ የሚቆይ የጤና ስርዓቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አለ ብለዋል፡፡
በክልሉ በትጥቅ የተደገፈ እንቅስቃሴ ያስከተለውን አለመረጋጋት ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ የቀረበለትን ሀሳብ አጽድቆ ወደ ተግባር ተገብቷል።
ይህንንም ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መመሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ትላንት በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ “በተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች” የተከሰተው የሰላም መደፍረስ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮችን ፈጥሯል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አቶ ተመስገን “ዘራፊ ቡድን” ያሏቸው አካላት የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን በመዝረፍ እና በማውደም ጭምር የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸመ ነው ብለዋል፡፡
የአለም ጤና ድርጅትና አጋር ድርጅቶች ስራቸውን እንዲቀጥሉ እና በክልሉ የጤና እርዳታ እንዳይቋረጥ ያስችል ዘንድ ዶ.ር ቴዎድሮስ በመልዕክታቸው የጤና ስርዓቱ ጥበቃ እንዲደረግለት ጠይቀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ “ለሰላም ጥሪ እናቀርባለን” ሲሉም በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መመሪያ ዕዝ ሰብሳቢው ገልጸዋል።
ከአለም ጤና ድርጅት በተጨማሪ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ዋና ጸሃፊ አንቶኒ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ሁኔታ ግን እንዳሳሰባቸው መግለፃቸው የሚታወቅ ነው። አስ