አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 11፣ 2014 ዓም:- “በአማራ ክልል ሁነኛ የሆነ የሲሚንቶ ፋብሪካ አለመኖሩ እጅግ የሚያስገርም ብቻ ሣይሆን ሁላችንንም ሊቆጨነንና ሊያንገበግበን የሚገባ ጉዳይ ነው” ሲሉ የአማራ ክልላዊ መንግስት የማዕድን ልማት ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሌ አበበ ተናገሩ።
ሃላፊው ይህን ያሉት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ማዕድን ልማት ሀብት ቢሮ ከዘንዘልማ ትሬድንግ ጋር የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ ይፋዊ የምርት ፈቃድ ስምምነት ተበተፈራረሙበት ወቅት ነው።
በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው የፊርማ ስርዓቱን ያከናወኑት የቢሮ ሃላፊው በበኩላቸው እስከ አሁን ድረሥ በተደረገው ጥናትና ምርምር በአምስት ዘርፍ የሚመደቡ ከ35 በላይ ማዕድናት እንዳሉ ገልፀው ጥናቱን ይበልጥ አጠናክሮ በማስኬድ ዕምቅ የሆነውን እና ገና ያልተዳሰሰውን መጠነ ሰፊና ዓይነተ ብዙ ማዕድናት በሚገባ ማልማት ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።
በክልሉ የኮንስትራክሽን የኢንዱሥትሪ፣ የሃይል አመንጪ፣ የጌጣጌጥና የከበሩ እንዲሁም ብረት ነክ ማዕድናት ያሉ ሲሆን ዘርፉን በውል ተረድቶ ወደ ሥራ በማሥገባት በኩል ግን ቀጣይ ሰፊ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ እጅግ ሰፊ ክምችት ያለው ለሲሚንቶ ማምረቻ ግበአትነት የሚውሉ ማዕድናት ያሉ ቢሆንም እስከአሁን ድረስ ግን በክልሉ ሁነኛ የሆነ የሲሚንቶ ፋብሪካ አለመኖሩ እጅግ የሚያሥገርም ብቻ ሣይሆን ሁላችንንም ሊቆጨነንና ሊያንገበግበን የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ከባለፉት አንድ ዓመት ተኩል ጀምሮ ለተለያዩ ማዕድናት ልማት ፍቃድ እየተሰጠ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ለሰባት ካምፓኒዎች የምርመራ ፍቃድ መሰጠቱን አንስተዋል። በረንታን ሲሚንቶ ፋብሪካን ጨምሮ ሁለት ፋብሪካዎች የምርት ፈቃድ በመውሰድ አስፈላጊውን ሥራ እየሠሩ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በትናንትናው እለት የሥራ ማስጀመሪያ ስምምነት የተፈራረመው የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ340 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተቋቋመ ፋብሪካ ሲሆን በቀጣይ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ማምረት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
ፋብሪካው አሁን ባለበት ደረጃ አስፈላጊውን የመንገድ ሥራ እና የፋብሪካ መትከያ ቦታ ጠረጋ፣ የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የማሽን ግዥ፣ የኦፕሬተር ተከላና መሰል ውሎችን ሲኖማ ከሚባል የውጭ ሀገር ካምፓኒ ጋር በመፍጠር ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል።
የሲሚንቶ ግብይትን እያዛቡ ያሉት አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ከግብይት ውጪ መደረጋቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ሰኔ 4 በሰጡት መግለጫ በግንባታው ዘርፍ ዋነኛ ግብዓት የሆነው ሲሚንቶ ግብይቱ ኢኮኖሚያዊ ባልሆኑ ሰውሰራሽ ምክንያቶች እየተዛባ ዋጋውም ከጊዜ ወደጊዜ እየናረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ለግብይቱ ችግር ውስጥ መውደቅ መንስኤ ከሆኑት ውስጥ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ዋነኛው መሆኑን ሚኒስትሩ አክለው ገልፀዋል፡፡
በሀገራችን ካሉ 13 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ውስጥ ከአንዱ በስተቀር እያመረቱ ያሉት ከማምረት አቅማቸው በአማካይ 50 በመቶ በታች መሆኑንም የተገለፀ ሺኆን ይህንን ለመሻሻል በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም ውጤት ባለመምጣቱ በግብይቱ ላይ እየተስተዋለ ያለው ችግር ሊቀጥል ችሏል ብለዋል፡፡አስ