ዜና፡ በትግራይ የምግብ እርዳታ በመቋረጡ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች መጨመሩ አሜሪካ ድጋጤ ፈጥሮብኛል ስትል ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23/2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ የረድኤት ድርጅቶች የምግብ እርዳታ አቅርቦታቸውን በማቋረጣቸው ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተዘግቧል። አሶሼትድ ፕሬስ በትግራይ የሚገኙ ባለስልጣናት በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች የምግብ እርዳታ ከተቋረጠ ወዲህ 728 ሰዎች መሞታቸውን ገልጸውልኛል ሲል ዘግቧል።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ለዜና አውታሩ በላከው የኢሜይል መልዕክት በእርዳታው መቋረጥ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች መጨመሩ ድንጋጤ እንደፈጠረበት አስታውቋል። እርዳታ ስርጭቱን የማቆም ውሳኔ እጅግ መራራ መሆኑን የገለጸው ተራድኦ ድርጅቱ በየትኛውም ሀገር ተፈጽሟል ተብሎ የማይገመት መጠን ያለው የምግብ እርዳታ በኢትዮጵያ መሰረቁን አመላክቷል። በምግብ እጦት ከሚሰቃይ ህዝብ ጉሮሮ ስርቆት መፈጸም ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑ ባሻገር ነገሩ ከአይምሮ በላይ ነው ሲል በአጽንኦት ኮንኗል።

በትግራይ ከምግብ እጦት ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የተመለከቱ ዘገባዎች አዲስ ስታንዳርድ በተለያዩ ግዜያት መዘገቡ ይታወሳል። በትላንትናው ዘገባ በአብይ አዲ መጠለያ ካምፕ ብቻ በረሃብ ሳቢያ ህጻናተ የሚገኙበት 27 ሰዎች መሞታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። የሟቾች ቁጥረ እጅጉን እየጨመረ መምጣቱን የመጠለያው አስተባባሪ ታደሰ ይልማ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.