አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18/2015 ዓ.ም፡- በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ እየሰራች እያለ የተወሰነ ወራት የወር ደመወዝ ክፍያ አልተከፈለኝም በሚል ምክንያት ቂም ይዛ አሰሪዋን በመደብደብ ህይወቷ እንዲያልፍ ያደረገች ግለሰብ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ መደረጉን የፍትህ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
ግለሰቧ ወንጀሉን የፈፀመችው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አስኮ አዲስ ሰፈር ሊዝ መንደር አካባቢ፣ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም ሲሆን አሰሪዋ ላይ በፈፀመችው አሰቃቂ ወንጀል በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ እንዲሁም ማህበራዊ መብቶቿ ለዘወትር እንዲሻሩ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኖባታል፡፡
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አበቡ ሙላቴ የተባለችው ተከሳሽ በቤት ሰራተኝነት እየሰራች እያለ የተወሰነ ወራት የወር ደመወዝ ክፍያ አልተከፈለኝም በሚል ምክንያት ቂም ይዛ ሟች በተቀመችበት በብረት ዘነዘና ጭንቅላታቸውን በመምታት ሟች ስትወድቅ በድጋሜ በብረት ዘነዘናው አንገታቸውን በመምታት እና በቢላዋ በመውጋት ህይወታቸው እንዲያልፍ ያደረገች በመሆኑ በፈፀመችው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባታል፡፡
ተከሳሽም ክሱ ተነቦላት የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ ያለች ሲሆን፣ ተከሳሿ የተከሰሰችበትን የወንጀል ድርጊት እንደ ክሱ ሙሉ በሙሉ ያመነች በመሆኑ ባመነችው መሰረት በተከሳሿ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ይሰጥልኝ ሲል ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ተከሳሿ በተከሰሰችበት ድንጋጌ ስር በዝርዝር ያመነች በመሆኑ ባመነችው መሰረት ጥፋተኛ ናት ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ጉዳዩን የተመለከተውም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም በተከሳሿ ላይ በደረጃ 2 እርከን 39 ስር መነሻ ቅጣት በመያዝ፣ ተከሳሽ ወንጀሉን ያመነች በመሆኑ፣ 1 የቅጣት ማቅለያ ተይዞላት በእርከን 38 ስር በማሳረፍ ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል በሚል በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ እንዲሁም ማህበራዊ መብቶቹ ለዘወትር እንዲሻሩ ሲል ወስኖባታል፡፡