ዜና፡- በስድስት ክልሎች በሚገኙ 158 ወረዳዎች ውስጥ ከ399 ሺሕ ሄክታር በላይ በለማ ስንዴ ሰብል ላይ የዋግ በሽታ መከሰቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ

ዋግ የመታው የስንዴ ሰብል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2015 ዓ.ም፡- የስንዴ ዋግ በሽታ ስንዴ አምራች በሆኑት በደቡብ፣ በሲዳማ፣ በአማራ፣ በቤንሻጉል ጉምዝ እንዲሁም በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች በአጠቃላይ ከ399 ሺሕ ሄክታር በላይ በለማ ስንዴ ማሳ ላይ መከሰቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ በላይነህ ንጉሤ ለአዲስማለዳ እንደገለፁት፤ በሽታውን ለመከላከል እስካሁን 308 ሺሕ ሊትር የኬሚካል ርጭት ተካሄዷል፡፡ በዚህም የከፋ ጉዳት እንደማያጋጥም ተናግረዋል። አያይዘውም ከ387 ሺሕ ሄክታር መሬት በላይ በኬሚካል ርጭት የመከላከል ሥራ መሠራቱን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ ሆኖም የኬሚካሉ ዋጋ መወደድ በአርሶ አደሮች ላይ ጫና ሳይፈጥር እንዳልቀረ ጠቁመዋል።

ይህ ዜና የተሰማዉ በኢትዮጵያ በዘንድሮ መኸር ምርት ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይገኛል ተበሎ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት ነዉ፡፡ በወረሃ መስከረም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደምትጀምር አስታወቀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በቀጣይ ዓመታት በሚሊየን ኩንታል የሚቆጠር የስንዴ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ታስቧል ብለዋል፡፡

አሁን የተከሰተዉ በሽታ በዚህ እቅድ ላይ ሊያስከትለዉ የሚችለው ጫና ባይገለጽም ሰብልን በተለይ ስንዴን የሚያጠቃዉ የስንዴ ዋግ የሚባለው በሽታ መተላለፍያው መንገድ በፈንገስ አማካኝነት ሲሆን ይህ በሽታ የስንዴውን የቅጠል አካሉን፣ ግንዱን በማጥቃት እና ቡቃያዉ ቢጫ እንዲሆን በማድረግ ምርትና ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ያደርጋል።

ሥራ አስፈጻሚው በላይነህ ንጉሤ እንደሚሉት በኦሮሚያ ክልል ከ372 ሺሕ ሄክታር መሬት በላይ በሽታው የተከሰተ መሆኑንና፣ በአንጻሩ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በጣም ትንሽ ሄክታር መሬት ላይ የተከሰተ መሆኑን አመላክተዋል። የበሽታው ምክንያት በዋናነት የሰብል ድግግሞሽ በመሆኑም፣ በሽታውን ለመከላከል ከኬሚካል ርጭቱ ይልቅ ሰብል ማፈራረቅ ተመራጭ መሆኑ ነው የተገለጸው።

ከዋግ በሽታ በተጨማሪም ሌሎች በሽታዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ የተጠቆመ ሲሆን፣ “ኤርፎዛሬን” የተባለው በሽታ በቀጣይ ዓመት ሌላው አስጊ የስንዴ በሽታ ሊሆን ይችላል ተብሏል። ይህ በሽታ ቀድሞ የነበረ ቢሆንም፣ ምልክቶቹ በተለያዩ ክልሎች እየታዩ ያሉ እና እጅግ አሳሳቢ መሆኑ ተመላክቷል።

በሽታው በምርት ላይ የሚያደርሰውን የጉዳት መጠን ለመለየት ጥናት እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት በላይነህ፣ ይህም የመስክ ባለሙያዎች ጥናቱን ሲጨርሱ የሚታወቅ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል። ከኬሚካል ርጭቱ ባለፈ በሽታ ሊቋቋሙ የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎችን አርሶ አደሩ የተጠቀመበት ሁኔታ በመኖሩም የጉዳት መጠኑን ሊያቀለው እንደቻለ ተመላክቷል።

በሽታው ቀድሞም የነበረ በመሆኑ አርሶ አደሩ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ እንደነበር ያነሱት ሥራ አስፈጻሚው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ካልደረሰባቸው አካባቢዎች በስተቀር፣ ኬሚካሉ ውድ ቢሆንም በኹሉም ቦታ መዳረሱን ነው የገለጹት።

የኬሚካል ርጭቱ የሚካሄደው የበሽታው ምልክት በታየበት ጊዜ መሆኑን በመጥቀስም፣ በክልሎች ያለው የበሽታው ስርጭት ከቆዳ ስፋታቸውና ከስንዴ አብቃይነታቸው ጋር ይያያዛል ብለዋል።

በአሮሚያ (ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች) እና አማራ ክልል (ሸዋሮቢት አካባቢ) ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል የተባለ ሲሆን፣ አካባቢዎች ደረቅ በመሆናቸው፣ የግሪሳ ወፎች ውሃ ወዳለበት ስለሚዘምቱ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመከላከል ከምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ የመከላከል ድርጅት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.