አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19/2015 ዓ.ም፡- በሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ በካርቱም የሚገኙ ዲፕሎማቲክ ኮሚዩኒቲ አባላት የኤምባሲዎቻቸውን በር በመቆለፍ በመውጣት ላይ እንደሚገኙ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ በርካታ ሀገራት ኤምባሲዎቻቸው ምንም አይነት አገልግሎት እንደማይሰጡ አሳውቀዋል፤ የካናዳ እና ፈረንሳይ በይፋ ኤምባሲዎቻቸውን ከዘጉ ሀገራት ይጠቀሳሉ።
በካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዛሬው እለት ስራውን ከካርቱም ወደ ገዳሪፍ በማዛወር በማከናወን ላይ መሆኑን በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ፌስቡክ አስታውቋል። በካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳመላከተው አካባቢው የውጊያ ቀጠና በመሆኑ፣ በአካባቢው የመብራት አገልግሎት በመቋረጡ፣ የምግብ ቁሳቁስ ለማግኘትም ሆነ ከኤምባሲ ወጥቶ ለመግባት ስላልተቻለ ስራውን ማቆሙን አስታውቋል። በዚህ ሁኔታ ዜጋን መርዳት ስለሚያዳግትና የዲፕሎማቶች ህልውናም አደጋ ላይ ስለሚወደቀ በኤምባሲው የተወሰኑ ሰራተኞች እዲቀሩ ተደርጎ አምባሳደሩን ጨምሮ ቀሪዎቹ ደግሞ ገዳሪፍ ከሚገኘው የቆንስላ ጽ/ቤት ጋር በመሆን ስራቸውን እያከናውኑ ይገኛሉ ሲል ገልጿል። ለዜጎች ሊደረግ የሚችለው ድጋፍም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑንም አመላክቷል።