አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11/ 2015 ዓ.ም፡- በጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የአገሪቱ መከላከያ ሀይል እና በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሀይል መካከል ለአምስት ተከታታይ ቀናት እየተካሄደ ባለው ውጊያ የሞቱ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን መረጃዎች እየደረሱን ነው ሲል የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሱዳን ገለፀ።
በሱዳን እየተካሄደ ባለው ውጊያ የበርካታ ሲቪሎችን ህይወት እየተቀጠፈ ነው ያለው ኢምባሲው በኢትዮጵያውያን ሞት እና ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፆ ለሟች ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ተመኝቷል።
ኢምባሲው በማህበራዊ ድረ ገፁ ባወጣው አችር መግለጫ ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ኢትዮጵያዊያን የተቻላቸውን ሁሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ኢምሳሲው በውጊያው የሞቱ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን መረጃ ከመስማቱ በቀር ስለ ሟቾች ብዛት እና ማንነት ምንም ያለው ነገር የለም፡፡
ነገር ግን ከትናንት በሱዳን ኦምዱርማን ከተማ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ አራት ኢትዮጵያዊያን በስቲያ ሚያዝያ 9፣2015 ዓ.ም. በጦር ጄት ጥቃት ህይወታቸው ማለፉን በሱዳን የሚኖር አንድ የጤና በለሙያ ነግሮኛል ሲል በስራት ራዲዮ ዘግቧል፡፡
በሱዳን 12 አመታትን የቆየዉና አስተያየቱን የብስራት ራዲዮ ምንጭና የጤና ባለሙያዉ አቶ ወንድወሰን ጌትነት ፤ ጥቃቱ የተፈፀመው ከትናንት በስቲያ 11 ሰዓት ከ 30 አካባቢ መሆኑን ጠቅሶ እስካሁን ከ 10 በላይ ኢትዮጵያዊያን በጦርነቱ ሞተዋል ብሏል፡፡ ምንጩ አክሎም በትናትናዉ እለት በካርቱም ( ጅሬፍ ) በደረሰ ሌላ ጥቃት ፤ ባለትዳሮች ህይወታቸውን ሲያጡ የሶስት አመት ህጻን ልጃቸዉ ከጥቃቱ ተርፏል ብሏል።
እንደ አቶ ወንድወሰን ገልፃ በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥበቃዎች በጦርነቱ ወቅት ከግዳጅ ቦታቸዉ በመነሳታቸዉ በታጣቂዎች በኢምባሲው ላይም ጥቃት ተፈፅሟል፡፡ ታጣቂዎቹ ገንዘብን ጨምሮ ዘረፋ መፈጸማቸዉንም በዘገባው ተካቷል።
ግለሰቡ ጥቃት አድራሾቹን ባያረጋግጥም የኤምባሲዉን ቅጥርግቢ ጥሰዉ በመግባት በግቢዉ በሱዳን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ባለቤት በሆነበት የመጠለያ ማዕከል ዉስጥ በነበሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ አጸያፊ ተግባራት ጭምር ተፈፅመዋል ሲል ገልጧል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ኢምባሲ በሱዳን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባለመሳካቱ የኢምሳውን አስታየት መካተት አልችልም፡፡
አምስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው ውጊያ እስካሁን ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ270 በላይ መድረሱን እና 2600 ባለይ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡አስ