አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም፡– በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የተደረሰው ስምምነት ተከትሎ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የተጎዱ የጤና ተቋማትን ለማደስ ጥረት እየተደረገ ነው። አለም አቀፉ የህጻናት አድን ድርጅት እና አጋሮቹ የዚህ ተግባር ተጠቃሽ ናቸው። በአማራ ክልል ላሊበላ አከባቢ የሚገኘው ዲቢኮ የጤና ማዕከል ትሩፋቱ ከደረሱት የጤና ተቋማት አንዱ ነው። የዲቢኮ የጤና ማዕከል በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት ከደረሰባቸው አንዱ ሲሆን የውስጥ ክፍሎቹን ገባ ብሎ ለተመለከተ ሰው በጥይት የተበሳሱ የጣሪያ ቆርቆሮዎቹን በመመልከት የጦርነቱን ክብደት በምልክትነት መረዳት አያዳግተውም። የጤና ማዕከሉ በጦርነቱ ወቅት እንኳ የህክምና እርዳታ መስጫ ተደርጎ ተጎጂዎችን ለመርዳት አልበቃም፤ በውስጡ የነበሩ የህክምና መገልገያዎች ተዘርፈዋል፤ እንደ ተራ ነገር ተቆጥሯል።
የጤና ተቋሙ መጎዳት በአከባቢው የሚኖሩ ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸውን ብዙ ነገር እንዲያጡ አድርጓቸዋል። በአከባቢው የሚኖሩ ስድስት እናቶች ህክምና እርዳታ ባለማግኘታቸው መሞታቸውን የጤና ማዕከሉ ዳይሬክተር ማሩ ተስፋ ይገልጻሉ። የማዕከሉ አምቡላንስ በመሰረቁ ምክንያት እናቶች ወደ ጤና ማዕከሉ ለእርዳታ እንኳን መምጣት አለመቻላቸውንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
እንደ ዲቢኮ የጤና ማዕከል ሁሉ በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው እና አገልግሎት ለመስጠት የማይችሉ ከሶስት ሺ በላይ የጤና ማዕከላት በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አለም አቀፉ የህጻናት አድን ድርጅት ከአየርላንድ ረድኤት ድርጅት ባገኘው ድጋፍ ጦርነቱ ጉዳት ባደረሰባቸው አከባቢዎች ለሚኖሩ ወላጆች እና ህጻናት ነጻ የህክምና እርዳታ በቤተሰብ የጤና መድህን ፕሮግራም እየሰጠ ይገኛል።
የጤና መድህኑ እጅግ እንደረዳው የሚናገረው አስሜ የተባለ የአከባቢው ነዋሪ የጤና መድህን አገልግሎቱን በመጠቀም ባለቤቱ ከአራት ወራት በፊት ልጅ መገላገሏን ይገልጻል። ሁሉንም የምንፈልገውን አገልግሎት እዚሁ እንድናገኝ በአስችሎናል ብሏል። በርካታ ተመሳሳይ ታሪኮች በአከባቢው መስማት እይተለመደ መጥቷል። የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ አለም አቀፉ የህጻናት አድን ድርጅት እና አጋሮቹ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የጤና ተቋማትን ለመደገፍ ጥረት እያደረጉ ይገኛል። እየተሰጡ ያሉ ድጋፎቹም ለማዋለድ አገልግሎት የሚጠቅሙ መሳሪያዎች፣ የክትባት መድሃኒትን ለማሰቀመጥ በፀሐይ ብርሃን የሚሰሩ ማቀዝቀዣዎች፣ ፍራሾችና ብርድ ልብሶች፣ የአይቲ ቁሳቁስ እንዲሁም የጤና ማዕከላት ለሚሰሩ ባለሞያዎች ስልጠናዎች ይገኙበታል። በየአከባቢያቸው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ህጻናት እና እናቶችን ለመርዳት ቁርጠኛ የሆኑ የጤና ሰራተኞች ቢኖሩም የህክምና መርጃ መሳሪያ፣ የትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የመሳሰሉ በርካታ ችግሮች ግን ፈተና መሆናቸው ቀጥሏል። መረጃውን ከዩኒሴፍ ድረገጽ አገኘነው። አስ