ዜና፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት አምስት ሰዎች ሲሞቱ በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ተባለ

በአብዲ ቢያንስ @ABiyenssa

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3/2015 ዓ.ም፡- በምእራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉዱሩ ዞን ኡሙሩ ወረዳ መደበኛ ያልሆኑ የፋኖ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች ሲሞቱ በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፁ፡፡

ለደህንነቱ በመስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ በኡሙሩ ወረዳ የአጋምሳ ከተማ ነዋሪ፣ ጥቃቱ የተሰነዘረው ረቡ ግንቦት 30 2015 መሆኑን ጠቅሶ በከተማዋ እና በአቅራቢያ የሚገኙ አካባቢዎች ቤቶች መቃጠላቸውን፣ መዘረፋቸውን እና ንብረት መውደሙን ገልጿል።

 “የጥቃቱ ሰላባዎች ንፁሃን አርሶ አደሮች ናቸው፤ በርካታዎች በጥቃቱ ሳቢያ ስፍራዉን ለቀው እየወጡ ነው፤ ታጣቂዎች አርሶ አደሮቹን ከእርሻ መሬታቸው ለማስለቀቅ ፈልገው ይሆናል” ሲል ነዋሪው ገልጿል።

ነዋሪው ባሳለፍነው አመት በተመሳሳይ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ገበሬውች ከስፍራው መፈናቀላቸውን ጠቅሷል፡፡ እንደ ነዋሪው ገለፀ ታጣቂዎቹ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ አቅራቢያ ወደምትገኘው ሀሮ ከተማ ሄደው እዚያው ይገኛሉ። ሀሮ ከአሙሩ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

ሌላኛው ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የአጋምሳ ከተማ ነዋሪ እንዳሉት ጉዲና ጉራቾ፣ ሶሪ ጁካር እና ታከለ ፉፋ የሚባሌ አርሶ አደሮች ከነ ባለ ቤቶቻቸው ተገድለዋል፡፡ ሶሪ እና ታከለ ከኡሙሩ ወረዳ ማካኖ ገጠራማ ቀበሌ የመጡ ነበሩ ብሏል ነዋሪው፡፡

በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ከአስር በላይ ንፁሃን በአቅራቢያው ወደሚገኘው ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ነዋሪው አክሎ ገልጧል፡፡

የፋኖ ታጣቂዎች ይገኙበታል በተባለው በኪረሙ ወረዳ አቅራቢያ ጥቃቶች መቀጠላቸውን የገለፀው ነዋሪው ታጣቂዎቹ እንደ ጨፌ ሶርማ፣ ቦቃ፣ ማያ ጂኒና፣ ቆቆጴ፣ ቆሬ እና ዳረባ ባሉ መንደሮች የገበሬዎችን ቤት እያቃጠሉ ነው ብሏል።

በጥቃቱ የተነሳ በርካታ ነዋሪዎች ስፍራውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን እና  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጠለላቸውን በርካታ ነዋሪውች ለአለዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል፡፡  የክልሉ መንግስት ከቀጠለው ጥቃት አርሶአደሮችን እንዲጠብቅ ነዋሪዎቹ አሳስበዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.