አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25/ 2015 ዓ.ም፡- በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የአረርቲ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በ17 ቀበሌዎች የወባ ወረርሽኝ በሽታ መከሰቱን የወረዳዉ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
በምንጃር ሸንኮራ ወረዳና በከተማ አስተዳደሩ የወባ ተጠቂ የተገኘባቸዉ ቀበሌዎችም አረርቲ 01፣ አረርቲ 02፣ አረርቲ ዙሪያ፣ አጊራጥ፣ ኮርማ፣ አዳማ፣ ድሬ፣ ጨሌ፣ ጨረቻ፣ ኢራንቡቲ፣ ክርስቶስ ሰምራ፣ አከላል፣ ራራቲ፣ ዱበቱ፣ ሰቃዋጮ፣ ጮባና አሞራቤት መሆናቸዉ ተገልጧል፡፡
በወረዳዉና በከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት የተከሰተዉ የወባ ወረርሽኝ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑንም በመጥቀስ በበጀት ዓመቱ እስካሁን 140 ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸዉና በአንድ ሳምንት ብቻ 38 ሰዎች በበሽታዉ ተይዘዉ መገኘታቸዉ በሽታዉ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል የወረዳዉ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ ጎሳ ተስፋዬ ፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን በበሽታዉ ህይወቱ ያለፈ ሰዉ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በወረዳዉ 23 ቀበሌዎች የሚታወቁ የወባ የስጋት ቦታዎች እንደነበሩ ገልፀው በዚህ ዓመት ግን ስጋት ያልነበሩ በሰባት ደጋማ ቀበሌዎች ወረርሽኙ በመከሰቱ የስጋት ቀበሌዎቹ ወደ 30 ከፍ ማለታቸዉን ገልፀዋል፡፡
ከ2010 ዓ.ም ወዲህ በወረዳዉ የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልኩ ተከስቶ እንዳልነበር ያነሱት ም/ኃላፊዉ በህብረተሰቡ የአጎበር መጠቀም ልምድና ሌሎች የመከላከል መንገዶች በመቀነሳቸዉ እንዲሁም ከሌሎች ቆላማ አካባቢዎች በስራ ምክንያት ወደ ወረዳዉ የሚመጡ ሰዎች መበራከታቸዉ ለበሽታዉ መከሰት እንደምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡
ማህበረሰቡ የወባ በሽታን ለመከላከል የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አቶ ጎሳ ጠቅሰዉ ያሉትን አጎበሮች እናቶችንና ህፃናትን በማስቀደም መጠቀም፣ በአካባቢዉ ያሉ ለወባ ትንኝ መራቢያ አመቺ የሆኑ ዉኃ ያቆሩ ቦታዎችን በመለዬት ማፋሰስ እንደሚገባዉና ምልክትም ሲታይበት በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራና ህክምና በማድረግ በጤና ባለሙያ ትዕዛዝ መሰረት መድኃኒቶችን በአግባቢ መዉሰድ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ አስ