አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7/ 2015 ዓ.ም፡- በሚዲያ ጥፋት የተጠረጠሩ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡ የመንግሥት የጸጥታ አካላት በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና በማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ ካተኮረ እስርና ማዋከብ እንዲቆጠቡም ጠይቋል፡፡
ኮሚስኑ የሚዲያ አባላትንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ዒላማ ያደረገ እስር እና ወከባን በተመለከተ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችንና አባላትን፣ የሚዲያ አባላትንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ላይ ትኩረት ያደረገ እስር እና ወከባ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን አመላክቷል፡፡
በያዝነው ወር ውስጥ ብቻ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነው ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውን ጨምሮ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው ፣ ጋዜጠኛ አራጋው ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው፣ ጋዜጠኛ ጌትነት አሻግሬ፣ ጋዜጠኛ በየነ ወልዴ፣ ጋዜጠኛ ሰናይት አያሌው፣ ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ፣ እንዲሁም በማኅበረሰብ አንቂነት (Activist) እና በሚዲያ ሥራም የሚታወቁት መስከረም አበራ ለእስር ከተዳረጉት መካከል ናቸው ሲል የገለፀው መግለጫው ከፊሎች በእስር ወቅት ተገቢ ላልሆነ አያያዝ የተዳረጉ፣ ከፊሎች ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ እስር ተዳርገው የነበሩ እና፣ ከፊሎችም ከተለያየ ጊዜ መጠን እስር በኋላ የተለቀቁ ናቸው ብሏል፡፡
ኢሰመኮ በወንጀል የተጠረጠሩና በበቂ ሕጋዊ ምክንያት በቅድመ-ክስ ሊታሰሩ የሚገባቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሁኔታም በሕግ በተመለከተው መንገድ ብቻ በጥብቅ ጥንቃቄ አንዲፈጸምና የተጠረጠሩ ሰዎችን ሁሉ ከምርመራ በፊት ከማሰር እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡
በተጨማሪም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 (የሚዲያ አዋጅ) መሠረት በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፣ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ-ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑ በግልጽ የተደነገገ መሆኑን ጠየቀሷል፡፡ ጨምሮም በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር መለቀቅ እንዳለባቸው ገልጧል፡፡
መግለጫው መንግሥት የወንጀል ተግባሮችን ሁሉ የመከላከል፣ የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና የማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚያተኩር እስር ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብቶች ላይ የሚያስፈራራ፣ የሚያሸማቅቅ እና የሚገድብ ውጤት እንዳይኖረው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡አስ