ዜና፡ በመዲናዋ የቱሪስቶች ደህንነት ለማስጠበቅ የቱሪስት ፖሊስ ሊቋቋም መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/ 2015 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ ከተማ የቱሪስቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ የቱሪስት ፖሊስ ለማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ ደስታ ሎሬንሶ፣ ስራዎችን ለማሳለጥ በቅርቡ የአዲስ አበባ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ይመሰረታል ያሉ ሲሆን ለዚህ ምክር ቤት የሚሆን የማቋቋሚያ ደንብ ጸድቋል ሲሉ ለኢቢሲ ተናግረዋል። አክለውም  የማቋቋሚያ ደንብ የማዘጋጀት እና በአወቃቀሩም ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የመወያየት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

ይህን ደንብ መነሻ በማድረግም ከ50 በላይ ከቱሪዝም ጋር የተያያዘ ስራ ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና በሃገር ውስጥ ያሉ አጋር አካላትን ያካተተ ምክር ቤት ይቋቋማል ብለዋል። የከተማዋን ቱሪዝም ለማሳደግ ከነዚህ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ሃላፊው አክለው አንስተዋል። በተለይም፣ በጸጥታ እና ሰላም ረገድ ስራዎች በከፍተኛ ደረጃ በትብብር እንደሚሰሩ እና በቅርቡ አገራችን የደረሰችበት የሰላም ስምምነትም ለዚህ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

በመረጃ መስጠት ረገድም ቱሪስቶች መረጃዎችን በአግባቡ ሊያገኙባቸው የሚችሉባቸው የመረጃ ማዕከሎች ከተማው ውስጥ በስፋት እንዲገነቡ እና ዲጅታል በሆነ መንገድ መረጃዎችን ለቱሪስቶች ተደራሽ ለማድረግ በዚህ ዘርፍም ቢሮው እንቅስቃሴዎችን እያረገ መሆኑ ተገልጿል።

ለቱሪስት ታክሲዎች እና አስጎብኝዎችም በየጊዜው ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስልጠና እንደሚሰጣቸው እና አገልግሎት አሰጣጣቸውም እንደሚፈተሽ አክለው ተናግረዋል። አሁንም ዘርፉ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሰፊ ክፍተት እንዳለ ያነሱት ኃላፊው፣ አዳዲስ አገልግሎት ሰጭዎችም ፍቃድ የሚያገኙበት እና ወደ ስራ የሚገቡበት መንገድ ተመቻችቷል ብለዋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.