አዲስ አበባ፣ ጥር 20/ 2015 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከቀኖና እና ከእውቅናዬ ውጭ የሆነ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት እና ጳጳሳት ሹመት ተስጥቷል በተባለው ጉዳይ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባካሄደው አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ፣ ሲመቱን በሰጡ ሊቀጳጳሳት እና ተሿሚዎች ላይ ያስተላለፈውን የውግዘት ውሳኔ ተከትሎ ውግዘቱ የተላለፈባቸው ሊቀጳጳሳት እና ተሿሚዎች “በእኛ ላይ የተላለፈው ውግዘት ባዶ ነው” ሲሉ የሲኖዶሱን ውሳኔ ውድቅ አድርገውታል።
ሊቀጳጳሳቱ እና ተሿሚዎቹ ትላንት በሰጡት መግለጫ የሲኖዶሱን ውሳኔ እንደማይቀበሉ በመግለፅ ውሳኔው በእኛ በሶስቱ ሊቀጳጳሳት እና በተሿሚወቹ ላይ ብቻ ሳይሆን ለቤተክርስቲያን ለሚቆረቆሩ እና የሚተጉትን ካህናት እንዲሁም ዲያቆናት ከቤተክርስቲያን አርቆ በቤተክርስቲያን ውድቀት የተለመደ ስጋዊ ምቾታቸውን እና ጎጠኛ ፍላጎታቸውን ለመምራት እንዲመቻቸው ነው ሲሉ ኮንነውታል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከቀኖና እና ከእውቅናዬ ውጭ የሆነ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት እና ጳጳሳት ሹመት ሰጥተዋል ባለችው በብጹእ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብጹእ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና ብጹእ አቡነ ዜና ማርቆስ ላይ እና 25 ተሿሚዎች ላይ ነው የውግዘት ውሳኔ ያስተላለፈችው።
አቡነ ሳዊሮስ በመግለጫቸው “እኛ የሰጠነው ሲመተ ጵጵስና የቤተክርስቲያኗን ህግጋት በጠበቀ መልኩ ነው” ሲሉ የጠቆሙ ሲሆን አክለውም፣ ይልቁንስ በእኛ ላይ የውግዘት ውሳኔ ካስተላለፉት ሊቀጳጳሳት ውስጥ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና በጣሰ መልኩ የጵጵስና ሹመት ያደረጉ ሊቃነጳጳሳት እንዳሉ እያወቁ በጎጠኞች ድጋፍ ታልፈዋል ሲሉ ወቀሳቸውን አስቀምጠዋል። በመሆኑም ውግዘቱ እውነተኞች አባቶች ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዳይገቡ ለመከላከል የተደረገ ነው ብለዋል።
በውግዘቱ ከተላለፉ ውሳኔዎች ውስጥ ምንም አይነት መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ እንዲሁም የቀብር አገልግሎት እንዳያገኙ መባሉ ከሃይማኖታዊነት አልፎ ሰብአዊነት የሚጋፋ እና ዜግነትን የሰረዘ ነው ሲሉ ተችለውታል።
በተጨማሪም አቡነ ሳዊሮስ በመግለጫቸው የሶስት ቀናት ሱባኤ ከታወጀ በኋላ ሱባኤው ሳይጠናቀቅ እና የመንፈስ ቅዱስን መልስ ሳይጠብቁ በሲኖዶሱ እንደተገለጸው በማህበራዊ ሚዲያ ጫና ተነሳስተው ተገቢ ያልሆነ ውግዘት አስተላልፈዋል ሲሉ በቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ የተሰጠውን ውሳኔ አጣጥለውታል።
ሲኖዶሱ ከቀናት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ካካተታቸው ውግዘቶችም መካከል ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን ከዲቁና ጀምሮ ያለውን ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻርና ማዕረጋቸውን በማንሳት እንደለያቸውና ከጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው “አቶ” እየተባሉ እንዲጠሩ መወሰኑን ይታወሳል።
በቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተክርስቲያን እንደለያቸው አጽንኦት ሰጥቶ ይፋ አድርጓል። የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ አውግዞ የለያቸው አባቶች ይመሯቸው በነበሩ አህጉረ ስብከቶች ሌሎች ብፁዐን አባቶች እንዲመደቡም ወስኗል፡፡ አስ