አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11/2015 ዓ.ም፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ኦቻ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያመለክተው ሰባት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የኮሌራ ወረርሽኝ ሊያጠቃቸው ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ እንዳስታወቀው ኮሌራ 94 ሰዎች ገድሏል። እስካሁን 6ሺ 157 በኮሌራ የተጠቁ ሰዎች መኖራቸውንም ጠቁሟል።
ወረርሽኙ በደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች በስፋት መሰራጨቱን የጠቆመው ሪፖርቱ በ54 ወረዳዎች እና ከስድስት ሺ በላይ ቀበሌዎች ላይ መዛመቱን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ የአሁኑ አይነት ለበርካታ ወራት የቆየ እና በታሪኳ የተመዘገበ የኮሌራ ወረርሽኝ አይታወቅም ያለው ተመድ በሪፖርቱ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የተመዘገበው በነሃሴ ወር 2014 እንደነበር አውስቷል። በሚያዚያ 2023 አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊየን የኮሌራ ክትባት በመላ ሀገሪቱ መሰራጨቱን ሪፖርቱ አመላክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ኦቻ ለኮሌራ ወረርሽኙ እየሰጠ ያለው ምላሽ በበቂ ፈንድ እጥረት፣ ውስን አጋሮች ብቻ መኖር እና ተያያዥ ጉዳዮች እንቅፋት እንደሆኑበት እና በሚገባ እንዳያከናውን እንዳደረጉት አስታውቋል።
ሀገራዊ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በበናፀማይ ወረዳ ብራይሌ ከተማ በይፋ መጀመሩን የጤና ሚኒስትር ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ዘመቻውን ሲያስጀምሩ ባስተላለፉት መልእክት ባለፉት አመታት መከላከልን መሰረት ባደረገው የጤና ፖሊሲ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸዉን አስታውቀው በተለይም የእናቶችና ህፃናትን ጤና ከማሻሻል፣ ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከልና መቆጣጠር ረገድ አመርቂ ውጤቶች ቢመዘገቡም ዛሬም ድረስ ኮሌራን ጨምሮ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።